ቀጥታ፡

የብልጽግና ትርክት እያንዳንዱን ዜጋ፣ ቤተሰብ እና መንደር ካልነካ የተሟላ አይሆንም - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ መስከረም 29/2018(ኢዜአ)፡- የብልጽግና ትርክት እያንዳንዱን ዜጋ፣ ቤተሰብ እና መንደር ካልነካ የተሟላ ሊሆን አይችልም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በክረምት በጎፈቃድ መርሐ ግብር በሀላባ እና ከምባታ ዞኖች የተገነቡ ሞዴል የገጠር መንደሮችን አስረክበዋል።

በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ እነዚህ መንደሮች የአርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮችን ሕይወት ለማሻሻል የምናደርገው ጥረት ተስፋ ሰጪ ጅማሮ ናቸው።


 

በሀገር ደረጃ ብልጽግናን ማረጋገጥ አለብን ስንል እያንዳንዱ ዜጋ ከነበረበት የኑሮ ዘዬ ወደ ተሻለ ደረጃ ማደግ አለበት ማለት ነው ሲሉም አስረድተዋል።

አክለውም፤ የብልጽግና ትርክት እያንዳንዱን ዜጋ፣ እያንዳንዱን ቤተሰብ፣ እያንዳንዱን መንደር ካልነካ የተሟላ ሊሆን አይችልም ነው ያሉት።

የብልጽግና ትርክት የተሟላ የሚሆነው በገጠርም በከተማም በከፍተኛ የኑሮ ደረጃ ያሉትንም እጅ አጠሮችንም የሚያቀራርብና ወደ መካከለኛ የሚያመጣ ሲሆን ነው ብለዋል።

በከተማ ደረጃ የከተማ ኮሪደር ብለን ላለፉት ዓመታት ያረጁ ቤቶችን ወደ አዲስ መንደሮች መለወጥ ችለናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በከተማ ላይ የሠራነውን ሥራ ወደ ገጠር ካላመጣነው በስተቀር በከተማ ብቻ ሠርተን ብልጽግናን ልናረጋግጥ አንችልም ሲሉ አስገንዝበዋል።


 

ስለዚህ አብዛኛው የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ አሁንም ገጠር ውስጥ ስለሚኖር፤ ገጠሩን መቀየር ያስፈልጋል ሲሉ በአጽንኦት ገልጸዋል።

ከነበረው የኑሮ ዘዬ ከፍ ያለ ገጠር መፍጠር አለብን የሚል ትልም ነበረን፤ ለዚህም ዘንድሮ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ አምስቱም ዞኖች ሥራ ተጀምሯል ብለዋል።

የምንሠራቸው ቤቶች የአንዱ ቤተሰብ ቤት ሦስት መኝታ ክፍሎች፣ በቂ ሳሎን፣ ከጓሮም ከፊትም እርሻዎች ያሉት፣ እንደሰለጠነው ዓለም ከብቶች የሚኖሩበትና የሚመገቡበት ቦታ ተለይቶ የተዘጋጀ መሆኑንም አብራርተዋል።


 

እያንዳንዱ ቤት ባዮ ጋዝ፣ የጸሀይ ሀይል ማመንጫ(ሶላር)፣ ውሃ፣ መብራት፣ መጸዳጃ ቤት እንዲሁም ወተት፣ እንቁላል፣ አትክልትና ሌሎችም የግብርና ምርቶች ከጓሮው የሚያገኝበት ምቹ ሁኔታ መኖሩን ጠቁመው ይህ ለአርሶ አደሮች በጣም ትልቅ ትርጉም ያለው ነገር ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም