ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የዘመናት ችግሮቿን ተሻግራ ወሳኝ ውጤቶች ያስመዘገበችበት የታሪክ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች 

አዲስ አበባ፤ መስከረም 28/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የዘመናት ችግሮቿን ተሻግራ ወሳኝ ውጤቶች ያስመዘገበችበት የታሪክ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች ሲሉ የብልፅግና ፓርቲ የፌዴራል ተቋማት  አስተባባሪ  ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ተስፋዬ  ቤልጂጌ (ዶ/ር ) ገለጹ።  

የኢኮኖሚ ብልፅግና ክላስተር የ2017 በጀት ዓመት የፖለቲካ እና አደረጃጀት ስራዎች አፈጻጸም የወረዳዎች እውቅና  አሰጣጥ መርሃ ግብር እየተካሄደ ነው ፡፡


 

የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የፌዴራል ተቋማት አስተባባሪ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ተስፋዬ ቤልጅጌ (ዶ/ር ) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ 2018 በጀት ዓመት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ወደ ወሳኝ ምዕራፍ የሚያሸጋግር መሰረት የተጣለበት ነው፡፡ 

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) የተበሰረበት ወቅት መሆኑን  አውስተዋል።

ኢትዮጵያ የከርሰ ምድር ሃብቷን አውጥታ ለመጠቀም የሚያስችሏትን ግዙፍ ፕሮጀክቶች ይፋ ማድረጓን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ በወሳኝ ምዕራፍ ላይ እንደምትገኝ አብራርተዋል።

ምክትል ሰብሳቢው ተስፋዬ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ የሚያስችል መሰረት እየተጣለ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በብልፅግና ፓርቲ መሪነትና በለውጡ መንግሥት አስተባባሪነት የዘመናት ችግሮቿን ተሻግራ ወሳኝ ውጤቶችን ያስመዘገበችበት የታሪክ ምዕራፍ ላይ እንደምትገኝም ተናግረዋል።

ብልፅግናን ለማረጋገጥ በሚደረገው እንቅስቃሴ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን ለማለፍ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ጠቁመው፤ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እልባት እንዲያገኙ የሚጠበቅብንን  ድርሻ መወጣት አለብን ብለዋል፡፡ 

ከአገልግሎት አሰጣጥ አኳያም ከህዝቡ የሚነሱ ጥያቄዎችን በአግባቡ ለመመለስ የተጀመሩ ስራዎችን ማጠናከር እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡ 

ብልፅግና ፓርቲ የዛሬ ብቻ ሳይሆን ዘመናት የሚሻገር ሀሳብና የሀሳብ ግልጽነት ያለው ነው ያሉት ምክትል ሰብሳቢው ተስፋዬ (ዶ/ር)፤ በፓርቲው እሴቶች፣ ፍልስፍናዎች፣ ሰነዶች ዙሪያ የጠራ የአመለካከት ግልጽነት መፍጠር እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የብልፅግና ፓርቲ ፍልስፍናዎችን በተመለከተ አራት መጽሐፎች መዘጋጀታቸውን ገልጸው፤ ዋናው መቆሚያችን መደመር ነው ብለዋል፡፡

የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የኢኮኖሚ ክላስተር ሰብሳቢ አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት  ለመሆን ያስቀመጠችው ግብ በትክክለኛ  መስመር ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡ 


 

የተፈጥሮ ጋዝ፣ የማዳበሪያ ፋብሪካ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ የተደረጉ ፕሮጀክቶች ለዚህ ማሳያዎች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ከታላቁ ሕዳሴ ግድብ እና ከተፈጥሮ ጋዝ ምርት የሚገኘው ሀይል የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ መሰረት በማስፋት የዜጎችን ኑሮ የሚያሻሽል መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

ፕሮጀክቶቹ የመንፈስ ልዕልናን የሚየጎናጽፉ፣ የጀመርነውን መጨረስ ካለምነው መድረስ እንደምንችል የሚያሳዩ የኢትዮጵያን ብልፅግና አይቀሬነት የሚያረጋገጡ ናቸው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያን የአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ ያስቀመጥነውን ግብ ለማሳካት በትክክለኛ መንገድ ላይ መሆናችንን ማሳያዎች ናቸው ብለዋል የኢኮኖሚና ክላስተር ሰብሳቢው አቶ መላኩ፡፡

ብልፅግና የተከታታይ ጥረቶችና ለውጦች ውጤት መሆኑን ገልጸው፤ ለተሻለ ስኬት ከዚህ በላይ መትጋት፣ ጅምሮችን መጨረስና አዳዲሶችን መፍጠር ይገባል ብለዋል፡፡

ከድህነት አዙሪት በመውጣት ራዕያችንን ዕውን ለማድረግ የፓርቲው አመራርና አባላት በፈጠራና በፍጥነት በእምርታ መስራት አለብን ሲሉም ገልጸዋል፡፡

የእውቅና መርሃ ግብሩ በወረዳዎች መካከል በአፈፃፀም ዙሪያ ልምድ ልውውጥ ለማድረግና የላቀ አፈጻጸም ለማስመዝገብ ትልቅ ሚና እንዳለውም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም