የደም አገልግሎትን በጥራት እና በስፋት ተደራሽ በማድረግ የሰውን ህይወት የማዳን ተግባር ይጠናከራል - ኢዜአ አማርኛ
የደም አገልግሎትን በጥራት እና በስፋት ተደራሽ በማድረግ የሰውን ህይወት የማዳን ተግባር ይጠናከራል
ድሬዳዋ፤ መስከረም 28/2018(ኢዜአ)፦ከበጎ ፈቃደኞች የሚሰበሰበውን የደም አገልግሎት በጥራት እና በስፋት ተደራሽ በማድረግ የሰው ህይወት የማዳን ተግባር እንደሚጠናከር የኢትዮጵያ የደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ገለጸ።
"ዲጂታላይዜሽንና ፈጠራ ለጠንካራ የደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት" በሚል መሪ ሃሳብ ለሁለት ቀናት በድሬዳዋ የተካሄደው 13ተኛው የዘርፉ አመታዊ ጉባኤ ተጠናቋል።
የኢትዮጵያ የደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አሸናፊ ታዘበው በወቅቱ እንደተናገሩት የደም አገልግሎትን በጥራት እና በስፋት ተደራሽ በማድረግ የሰውን ህይወት የማዳን ተግባር ይጠናከራል።
በተያዘው በጀት ዓመትም ከበጎ ፈቃደኞች የሚሰበሰበውን ደም በማሳደግ ጤናማ ማህበረሰብ የመፍጠርና ህይወትን የመታደግ ስራ በትኩረት ይከናወናል ብለዋል።
ለዚህም ከፌደራል እስከ ከተማ የሚገኙ ማዕከላት፣ የክልሎችና የከተሞች የጤና ቢሮዎችና ተቋማት የተቀናጀ እና የተናበበ ስራ በመስራት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
ባለፈው ዓመት በመላ አገሪቱ ከሚገኙ በጎ ፈቃደኞች 424 ሺህ ዩኒት ደም መሰብሰብ መቻሉን አስታውሰዋል።
ጅምር አበረታች ስራዎች የተከናወኑ ቢሆንም አሁንም በአገር ደረጃ ካለው ፍላጎት አንፃር ብዙ ርቀት መጓዝ ይጠበቃል ብለዋል።
ለዚህ ስራ መሳካት ጠንካራ ተቋማት መገንባት፣ የደም ሰብሳቢዎችን አቅም ማሳደግ እንዲሁም በአገልግሎቱ ደረጃ የተጀመሩ ውጤት አምጪ ኢንሼቲቮችን በዲጂታል አሰራር የማጠናከር ስራ እንደሚሰራም አስረድተዋል።
በተጨማሪም የተደራጀ የዳታ አስተዳደር አሠራር መዘርጋት በተጨባጭ መረጃና አኃዝ ላይ የተመሰረተ ወሳኔ ለመስጠትም ትኩረት ተድርጓል ብለዋል።
የኢትዮጵያ የደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ወይዘሮ ጤናዬ ደምሴ በበኩላቸው ዘንድሮ የደም አሰባሰቡን በፍጥነትና በጥራት ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ ዘመናዊ የህክምና ማሽኖች ወደ አገልግሎት የሚገቡ በመሆኑ የተሻለ ውጤት ይመጣል ብለዋል።
በተያዘው ዓመት 550 ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ መታቀዱንም አስታውቀዋል።
የጉባኤው ተሳታፊዎችም በደም ዕጦት አንድም ዜጋ እንዳይሞት ለማድረግና የተጣለባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት በትኩረት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።