ቀጥታ፡

በፍትህ ተቋማት አስተማማኝና ደህንነቱ የተጠበቀ የመረጃ አያያዝ ስርአትን ማጠናከር ይገባል

ባህርዳር፤ መስከረም 28/2018(ኢዜአ)፦ በፍትህ ተቋማት አስተማማኝና ደህንነቱ የተጠበቀ የመረጃ አያያዝ ስርአትን ማጠናከር እንደሚገባ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሀሚድ አስገነዘቡ።

ዋና ዳይሬክተሯ ለአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች የዳኞች ጉባኤ በሳይበር ደህንነት ዙሪያ በባህር ዳር ከተማ ስልጠና ሰጥተዋል።

በስልጠናው ላይ የዳኝነት ስርአቱን ቀልጣፋና ዘመናዊ አሰራርን የተከተለ እንዲሁም የመረጃ አያያዝ ስርአት ደህንነቱ የተጠበቀ ማድረግ እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።

የዳኝነት አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎችና ሰራተኞችም ከዘመኑ ጋር የሚራመድ የዳበረ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም እንዲሁም አስተማማኝ የመረጃ አያያዝ ስርአትን የተገነዘቡ መሆን እንዳለባቸው አንስተዋል።


 

የተዘዋዋሪ ችሎት ዘመናዊ አሰራሮችን ተጠቅሞ በማካሄድ የህብረተሰቡን ጊዜ፣ ጉልበትና ወጪ ለመቆጠብ ዘመኑ የሚጠይቀውን እውቅትና ክህሎት በመላበስ ለህዝብ አገልግሎት መስጠት የሚገባ መሆኑንም ገልጸዋል።

በዚህ ረገድ የፍትህ ተቋማት ባለሙያዎችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት የሳይበር ደህንነት ፖሊሲና አዋጅን በአግባቡ በመረዳት ለተግባራዊነቱ በጋራ መትጋት እንዳለባቸው ዋና ዳይሯክተሯ አስገንዝበዋል።

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለም አንተ አግደው በበኩላቸው የዜጎችን የፍትህ ተደራሽነት ለማረጋገጥ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ችሎትን በስፋት ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።


 

በዚህም የሳይበር ደህንነቱ የተረጋገጠና የቨርቿል ችሎትን እስከታች ድረስ ተደራሽ ለማድረግ ዳኞችን በተከታታይ የማሰልጠን ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የአይሲቲ ዳይሬክተር መኳንንት አገኘሁ(ዶ/ር)፤ የክልሉን የችሎት ስርዓት በቴክኖሎጂ የታገዘና ወቅቱን የሚመጥን ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ ሲሰራ መቆየቱን አንስተዋል።

በተሰራው ስራም ከጠቅላይ ፍርድ ቤት እስከ ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች የኔትወርክ መሰረተ ልማት ዝርጋታ ተጠናቆ ወደ ትግበራ መገባቱን አስረድተዋል።

የሳይበር ደህንነትን አስተማማኝ ለማድረግም የሚበለጽጉ ቴክኖሎጂዎች ደህንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን በጥንቃቄ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

በባህር ዳር ከተማ እየተሰጠ የሚገኘው የአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች የዳኞች ጉባኤ ስልጠና ነገም የሚቀጥል ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም