ቀጥታ፡

በድሬዳዋ የህዝቡን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ  እየተከናወኑ የሚገኙ አበረታች ስራዎች መጠናከር አለባቸው- ቋሚ ኮሚቴው   

ድሬዳዋ ፤ መስከረም 28/2018 (ኢዜአ)፦በድሬዳዋ የህዝቡን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ እና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመፍታት እየተከናወኑ የሚገኙ  አበረታች ስራዎች መጠናከር እንዳለባቸው የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የከተማ፣ መሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታወቀ።

የከተማ፣ መሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ዛሬ በድሬዳዋ እየተከናወኑ የሚገኙ የመሠረተ ልማቶች እና የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።


 

የኮሚቴው አባላት የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና፣ የደረቅ ወደብና ተርሚናል፣ የድሬ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ አለም አቀፍ ስታዲዮም፣ የኮንቬንሽን ማዕከል እና የእመርታ ቤተ-መፅሐፍት በመጎብኘት ከአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ውይይት አካሄደዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መሐመድ አብዶ እንዳሉት በድሬዳዋ እየተገነቡ የሚገኙ መሠረተ ልማቶች የነዋሪውን የልማትና የአገልግሎት ጥያቄዎች በፍጥነትና በጥራት እንዲመለሱ የሚያግዙ ናቸው።


 

የመሠረተ ልማቶቹ መገንባት ድሬዳዋን በኢንዱስትሪ፣ የንግድና የኮንፈረንስ ቱሪዝም ዘርፎች ተመራጭ ያደርጋታል ብለዋል።

በተለይ በቅርቡ አገልግሎት መስጠት የጀመረው መሶብ  ድሬ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እንቅስቃሴ አበረታችና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑን በመግለፅ።

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ እሸቱ ተመስገን (ዶ/ር) በበኩላቸው በአስተዳደሩ ገቢን አሟጦ በመሰብሰብ፣ ህዝብንና ድርጅቶችን አስተባብሮ የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎች በአርዓያነት የሚጠቀሱ መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

እነዚህን አበረታች ስራዎች በላቀ ደረጃ ለማስቀጠል ሁሉም የአስተዳደሩ አመራሮች በትብብር መስራት አለባቸው ብለዋል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላቱ አቶ ፍቃዱ ጋሻው እና ወይዘሮ ታለፍ ፍትህአወቀ፣ በአመራሩ የተናበበ ቅንጅት የከተማ አገልግሎቶችን ለማዘመንና መሠረተ ልማቶችን ለማስፋፋት የተጀመረው ጥረት በላቀ ደረጃ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህና ቋሚ ኮሚቴው በድሬዳዋ ተገኝቶ ያደረገው የመስክ ግምገማ በቀጣይ የተሻለ ስራ ለመስራት የሚያነቃቃ መሆኑን ገልፀዋል።


 

በድሬዳዋ የተጀመሩ የመሠረተ ልማት ማስፋፊያ ስራዎችን በፍጥነት ለማጠናቀቅም ርብርቡ ይቀጥላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም