ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ክብርና ሉአላዊነት በላቀ ብቃትና ዝግጁነት የማስጠበቅ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ሌተናል ጄኔራል መሐመድ ተሰማ

ባሕርዳር ፤ መስከረም 28/2018 (ኢዜአ) ፡-  የኢትዮጵያን ክብርና ሉአላዊነት በላቀ ብቃትና ዝግጁነት የማስጠበቅ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል መሐመድ ተሰማ ገለጹ።

ሌተናል ጄኔራሉ  በየደረጃው ካሉ የዕዙ ከፍተኛ መኮንኖችና ኃላፊዎች ጋር በመምከር በግዳጅ አፈጻጸም ቀጣይ ተልዕኮዎችን በተመለከተ አቅጣጫ ሰጥተዋል።


 

የኢትዮጵያ የጀግንነት ታሪክ ከጥንት ጀምሮ አብሮ የዘለቀ እና አሁንም በላቀ መልኩ የቀጠለ መሆኑን አንስተው፤  የሰራዊቱ ጀግንነት፣ ግዳጅና ተልዕኮ የመፈፀም ብቃት የሚደነቅ ነው ብለዋል። 

በእድገትና ማንሰራራት እንዲሁም ስኬቶችን እያስመዘገበች ለቀጠለችው ኢትዮጵያ የሚመጥን ጠንካራ ሰራዊት መገንባቱን አንስተው፤  ክብርና ሉአላዊነቷን አስጠብቆ መዝለቅ የዚህ ትውልድ አደራ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም የቀደሙት አያቶች አኩሪ የጀግንነት ገድል ከነ ሙሉ ክብሯ ያስረከቡንን ሀገር እኛም በላቀ ክብርና ሞገስ ለቀጣዩ ትውልድ የማስረከብ ግዴታ አለብን ብለዋል።

በኢትዮጵያ ለጠላት አስፈሪና ለሀገር አኩሪ የሆነ ጠንካራና ዘመናዊ ሰራዊት መገንባቱን ያነሱት ሌተናል ጀነራል መሐመድ፤ በዚህ ረገድ የምስራቅ ዕዝ የሀገርን ክብርና ሉአላዊነት ለማስጠበቅ ለላቀ ሀገራዊ ተልእኮ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በአማራ ክልል  አንዳንድ አካባቢዎች በጫካ የሚንቀሳቀሰው ጽንፈኛ ቡድን በክህደት የጠላት ተልዕኮ ለማስፈፀም ቢሞክርም በዕዙ ጠንካራ እርምጃ እየተወሰደበት መሆኑን አረጋግጠዋል።

የምስራቅ እዝ በዚሁ የግዳጅ አፈፃፀም ጽንፈኛ ቡድኑን በመከታተል እርምጃውን አጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸው፤ በክልሉ  ዘላቂ ሰላምን ለማፅናት  ወታደራዊ እርምጃው የሚቀጥል መሆኑንም አፅንኦት በመስጠት አብራርተዋል።

ዋና አዛዡ እንዳመለከቱት፤ ከአማራ ክልል የፀጥታ ሀይል ጋር በመጣመር የሚደረጉት ስምሪቶች ውጤት ማምጣታቸውን አስታውሰው፣ በአሁኑ የክልሉ የፀጥታ ሀይል ራሱን ችሎ በመንቀሳቀስ አኩሪ ግዳጅ እየፈጸመ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል ።

በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሰው ጽንፈኛ ቡድን ዓላማ የኢትዮጵያን ጠላቶች ተልእኮ በመቀበል ሀገርና ህዝብን መውጋት መሆኑን ህዝቡ በአግባቡ የተረዳ በመሆኑ ከሰራዊቱ ጎን በመቆም አጋርነቱን እያሳየ መሆኑን እና ሰራዊቱ ተከታትሎ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ገልጸዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም