ስፔን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ትብብር አጠናክራ ትቀጥላለች -አምባሳደር ጉሌርሞ ሎፔዝ - ኢዜአ አማርኛ
ስፔን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ትብብር አጠናክራ ትቀጥላለች -አምባሳደር ጉሌርሞ ሎፔዝ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 28/2018(ኢዜአ)፡- ስፔን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል በኢትዮጵያ የስፔን አምባሳደር ጉሌርሞ ሎፔዝ ማክ-ሌላን ገለፁ።
በኢትዮጵያ የስፔን አምባሳደር ጉሌርሞ ሎፔዝ ማክ-ሌላን ስፔን ከኢትዮጵያ ጋር ለረጅም ጊዜያት በተለያዩ ዘርፎች በጋራ እየሰራች ነው ብለዋል።
ሁለቱ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋምና በሌሎች የልማት ስራዎች በጋራ እየሰሩ መሆኑን ገልፀዋል።
በስፔን ትብብር ማዕቀፍ በኩል የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ለማረጋገጥና ለማብቃት እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በዚህም በርካታ ሴቶች በኢትዮጵያ የልማት ጉዞ ውስጥ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል።
በጤናው ዘርፍ ከህክምና መሳሪያዎች ጀምሮ ብቁ ባለሙያዎችን ለማፍራት የሚያስችል ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ ልማትን ለማረጋገጥ ለምታደርገው ጥረት ስፔን ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥልም ነው ያስረዱት።
በሌላ በኩል ስደተኞችና ተቀባዩ ማህበረሰብ የንፁህ ውሃ አቅርቦት፣ የሶላር ኢነርጂና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎት እንዲያገኙ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር እየሰራን ነው ብለዋል።
ስፔን በቀጣይ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲያዊ ትብብር ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።