የብሔራዊ የብቃት ማረጋገጫ ማዕቀፍ ለተማሪዎች ውጤት መሻሻል የማይተካ ሚና እያበረከተ ነው- ትምህርት ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የብሔራዊ የብቃት ማረጋገጫ ማዕቀፍ ለተማሪዎች ውጤት መሻሻል የማይተካ ሚና እያበረከተ ነው- ትምህርት ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤መስከረም 28/2018 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ ብሔራዊ የብቃት ማረጋገጫ ማዕቀፍ ትግበራ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ጉልህ ፋይዳ እያበረከተ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ የሀገር አቀፍ የትምህርት ጥራት ማስጠበቂያ ማዕቀፍ በ2016 ዓ.ም በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቆ ተግባራዊ መደረጉ ይታወቃል።
የትምህርት ሚኒስቴር ዴኤታ አየለች እሸቴ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ማዕቀፉ የመምህራንን አቅም በስልጠና በመገንባት በተማሪዎች ውጤት ላይ ለውጥ እንዲመዘገብ እያደረገ ነው፡፡
ተማሪዎች ለትምህርታቸው ትኩረት እንዲሰጡ መነሳሳትን በመፍጠር ለትምህርት ጥራት መሻሻል ገንቢ ሚና እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።
ወላጆችም ልጆቻቸው ትምህርታቸውን በአግባቡ ተከታትለው የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንዲችሉ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ማድረግ አለባቸው ብለዋል፡፡
ይህንን ተከትሎ የብሔራዊ የብቃት ማረጋገጫ ማዕቀፍ ለተማሪዎች ውጤት መሻሻል የማይተካ ሚና እንዳለው አክለዋል፡፡
በተለይ ተማሪዎች በራሳቸው የመተማመን አቅምን እያዳበሩ የመጡበት እድልን የፈጠረ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የብቃት ማረጋገጫ ማዕቀፍ ትግበራ በትምህርት ሥርዓቱ ላይ እያመጣ የሚገኘውን ውጤት በማስመልከትም የትምህርት ቤት ርዕሳነ መምህራንና መምህራን አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የአዲስ ከተማ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር እንዳልካቸው ደጀኔ፤ የብቃት ማረጋገጫ ማዕቀፉ በመምህራንና ተማሪዎች የመማር ማስተማር ሥርዓት ላይ ገንቢ መነሳሳትን ፈጥሯል ብለዋል።
የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ በተማሪዎች ውጤት መሻሻል ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የመድኃኒዓለም አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ባርኪ ዴቲ፤ ማዕቀፉ የመምህራንና ተማሪዎችን ተግባቦት በማሳደግ ምቹ የመማር ማስተማር የሥነ-ምግባር ምኅዳር መፍጠሩን ተናግረዋል።