የገጠር ኮሪደር ልማት መንደሮች ተስፋፍተው ይቀጥላሉ-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የገጠር ኮሪደር ልማት መንደሮች ተስፋፍተው ይቀጥላሉ-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤መስከረም 28/2018 (ኢዜአ)፡- የገጠር ኮሪደር ልማት መንደሮች የገጠሩን አኗኗር የማሳደግ ሕልማችን አካል በመሆን ተስፋፍተው የሚሰሩ ይሆናል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ዛሬ በክረምት በጎፈቃድ መርሐግብር በሀላባ እና ከምባታ ዞኖች የተገነቡ ሞዴል የገጠር መንደሮችን አስረክበናል ብለዋል።
እነኚህ መንደሮች የአርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮችን ሕይወት ለማሻሻል የምናደርገው ጥረት ተስፋ ሰጪ ጅማሮ ናቸው ሲሉም ገልጸዋል።
ቤቶቹ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ የተገጠመላቸው፣ ለማብሰል ደግሞ ከእንስሳት እዳሪ ባዮጋዝ የሚጠቀሙ፣ የተለየ ሳሎን፣ መጸዳጃ እና ሰርቪስ ቤቶች የተሟላላቸው ናቸው ሲሉም አብራርተዋል።
ንጽህናን በሚያረጋግጥ እና የአኗኗር ደረጃን ከፍ በሚያደርግ አኳኋን የተለየ የእንስሳት በረት እንደተሠራላቸውም ጠቁመዋል።
እነዚህ የገጠር ኮሪደር ልማት መንደሮች የገጠሩን አኗኗር የማሳደግ ሕልማችን አካል በመሆን ተስፋፍተው የሚሠሩ ይሆናል ሲሉም አመላክተዋል።
ባለፉት ሰባት ዓመታት የክረምት በጎ ፈቃድ በከተሞች ለሚኖሩ ለችግር የተጋለጡ ወገኖች መኖሪያ ቤቶችን ስናቀርብ ቆይተናል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
አሁን ደግሞ በገጠር ኮሪደር ልማት የሥራውን እመርታ ወደገጠር አስፋፍተናል ነው ያሉት።
ግለሰቦች፣ድርጅቶች እና የዳያስፖራው ማኅበረሰብ እነኚህን ሥራዎች እንዲደግፉ እና እንዲሳተፉ አበረታታለሁም ብለዋል።
ባለፈው ጉብኝቴ ወቅት ያቀረብኩላቸውን የቤትሥራ በመወጣት በአጭር ጊዜ ውስጥ በራስ አቅም የሀምበሪቾ ተራራ ደረጃንም በእጥፍ ሠርተው ላጠናቀቁት አመራሮች ያለኝን ምስጋና አቀርባለሁ ብለዋል።
ወደፊትም የየአካባቢ አመራሮች ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተሠሩትን ሞዴል መንደሮች በመጪው ዓመት በየዞኑ ወደ100 ቤቶች እንዲያሳድጉ አሳስባለሁ ብለዋል።