ቀጥታ፡

የኒውክለር ኃይል የህክምና አገልግሎትን ማዘመንና ለጤና ተቋማት የኃይል አቅርቦት ተደራሽነትን ማስፋት ያስችላል-ጤና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤መስከረም 28/2018 (ኢዜአ)፡-የኒውክለር ኃይል የህክምና አገልግሎትን ማዘመንና ለጤና ተቋማት የኃይል አቅርቦት ተደራሽነትን ለማስፋት የሚያስችል መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሳህረላ አብዱላሂ ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ በኢትዮጵያ ከ30 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሀብት የሚፈስባቸው ሜጋ ፕሮጀክቶች እንደሚገነቡ መግለጻቸው ይታወቃል።

ከእነዚህ ሜጋ ፕሮጀክቶች መካከል ለሰላማዊ አገልግሎት የሚውል የኒውክሌር ማበልፀጊያ አንዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሳህረላ አብዱላሂ ለኢዜአ እንዳሉት፥በኢትዮጵያ በቀጣይ ዓመታት ከሚገነቡ ግዙፍ አህጉራዊ ፕሮጀክቶች መካከል የኒውክለር ሃይልን ለሰላማዊ አገልግሎት ለማዋል መታቀዱ ዘርፍ ብዙ ፋይዳ አለው።

ኒውክለር ለጤናው ዘርፍ የተለያዩ ስራዎች እንደሚውል በመግለጽ፤ የኒውክለር ሃይል ለካንሰር ህክምና እና ሌሎች የጨረራ ህክምና አገልግሎቶች ጉልህ አበርክቶ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

የህክምና መሳሪያዎችን ለማፅዳት፣ለመጠገንና በአየር ብክለት ምክንያት የሚከሰቱ በሽታዎችን ለመከላከል የኒውክለር ኃይል ፋይዳው የላቀ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ የተሟላ የካንሰር ህክምና የሚሰጡ ሆስፒታሎች ቁጥር ከሰባት እንደማይበልጥ የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ የኒውክለር ኃይል የካንሰር ህክምና አገልግሎትን ተደራሽነት ለማስፋትና ለማዘመን አጋዥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኒውክለር ኃይል የህክምና አገልግሎትን ከማዘመን ባለፈ የህክምና ተቋማትን የኃይል አቅርቦት ተደራሽነት ማስፋት ያስችላል ብለዋል፡፡


 

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አንዱዓለም ደነቀ በበኩላቸው፤ የጤና ሳይንስ ኮሌጁ የኒውክለር ህክምና ትምህርት ክፍልና የካንሰር ህክምና ማዕከል የኒውክለር ኃይልን እንደሚጠቀሙ ገልጸዋል፡፡

በኒውክለር ህክምና ትምህርት ክፍል ያሉ መሳሪያዎች የካንሰር፣ ልብና ኩላሊት ህመም ያሉበትን ደረጃና የጉዳት መጠን ለመለየት ያግዛል ብለዋል፡፡

የእንቅርት ህመሞችን ለማከም ወሳኝ መሆኑን በመጥቀስ፤ ለህክምናና ምርመራ አገልግሎት ጠቀሜታ ያላቸው ግብዓቶችን ለማምረት አስፈላጊ ግብዓት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ የኒውክለር ኃይልን ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል ማበልፀጊያ ሊገነባ መሆኑ ለዘመናዊ መመርመሪያ መሳሪያዎች የሚያገለግሉ አጭር ቆይታ ያላቸው ግብዓቶችን (ሪኤጀንቶች) በሀገር ውስጥ ለማምረት የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል።


 

የጅማ ዩኒቨርሲቲ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አህመድ ዘይኑዲን የኒውክለር ቴክኖሎጂ ተላላፊ ላልሆኑና ለተለያዩ ህክምናዎች ጥቅም ላይ ይውላል ብለዋል።

የኒውክለር ኃይል ለተለያየ የህክምና አገልግሎት ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑን አንስተው፥ በኢትዮጵያ የኒውክለር ማበልፀጊያ መገንባት ከኃይል ባሻገር ለህክምና ዘርፉ የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም