ቀጥታ፡

መንግሥት የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ የጀመራቸውን ተግባራት ለማሳካት ተሳትፏችንን እናጠናክራለን-የመዲናዋ ነዋሪዎች

አዲስ አበባ፤መስከረም 28/2018 (ኢዜአ)፡-መንግሥት የህዝብን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ የጀመራቸውን አበረታች ተግባራት ለማሳካት የበኩላቸውን ተሳትፎ እንደሚያጠናክሩ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጹ።

ስድስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት መስከረም 26 ቀን 2018 ዓ.ም ተካሂዷል።

የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ በመክፈቻ ስነ ሥርዓቱ የኢትዮጵያን ዘላቂ እድገት ለማረጋገጥ መንግስት በ2018 በጀት ዓመት በልዩ ልዩ መስኮች የያዛቸውን እቅዶች ለሁለቱ ምክር ቤቶች አቅርበዋል።

በበጀት ዓመቱ ለዜጎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ የሚኖራቸው ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገኙበት አብራርተዋል።

ከእነዚህም መካከል የቤት ግንባታ ማከናወን፤ የገጠሩን የሀገሪቱ ክፍል በልማት ማዘመን፣ የኮሪደር ልማት ስራን ማጠናከር፣ የዜጎችን የኤሌክትሪክ፣ የመንገድ፣ የንጹህ መጠጥ የውሃ ፍላጎትን ሊያሟሉ የሚያስችሉ የልማት ስራዎች ማከናወን የሚሉት ይገኙበታል።

ፕሬዝዳንት ታዬ ያቀረቧቸውን የመንግስት የትኩረት አቅጣጫዎች በተመለከተም ኢዜአ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን አነጋግሯል።

ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል አቶ ሠናይ አበባየሁ እንዳሉት፤ መንግስት በሀገሪቱ የተለያዩ የመሰረተ ልማት ስራዎችን በበጀት ዓመቱ በተሻለ መልኩ ለመስራት ወደ ተግባር መግባቱ የሚበረታታ ነው።

ይህም ኢትዮጵያን ወደ ላቀ ዕድገት ለማሸጋገር የተያዘውን ግብ የሚያሳካና የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ሰለሞን ሀብቴ በበኩላቸው፥ መንግስት በዚህ ዓመት ሊያከናውናችው ያቀዳቸው ሜጋ ፕሮጀክቶችና የተጀመሩ ልማቶች ለሀገርና ለትውልዱ ወሳኝ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አዲስ አበባን ጨመሮ ከተሞችን ለማዘመን እየተከናወነ ያለውን የኮሪደር ልማት በገጠሪቱ የሀገሪቱ ክፍል ለማስፋት የተጀመረው ስራ ሊጠናከር እንደሚገባ አንስተዋል።

በተለያዩ ጊዜያት የሚሰሩ የልማት ስራዎች አበረታች ውጤቶች እያስገኙ መሆናቸውን ማየት ችያለሁ ያለው ደግሞ መሀመድ መኪን አብደላ ነው።

በመንግስት ሊሰሩ የታሰቡ የልማት ስራዎች እውን እንዲሆኑ የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ ለመወጣት ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጧል።

ሞገስ አያሌው የልማት ስራዎች የሀገሪቱን ምጣኔ ሀብታዊ ግስጋሴ የሚያሳልጡ መሆናቸውን ተናግሯል።

ኢትዮጵያውያን በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድቡ ያስመዘገብነውን ስኬት በሌሎች ሀገራዊ ፕሮጀክቶች የማናሳካበት ምንም ምክንያት አይኖርም ሲል ተናግሯል።

መንግሥት የህዝብን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ እያከናወናቸው ያሉ አበረታች ተግባራት ከዳር እንዲደርሱ የበኩላቸውን ሚና ለመጫወት ዝግጁ መሆናቸውንም ነዋሪዎቹ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም