ቀጥታ፡

የመደመር መንግሥት መፅሐፍ አምራች ኢንዱስትሪው በፈጠራና ፍጥነት ወደ ተሻለ እመርታ እንዲሸጋገር መንገድ ያሳየ ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 28/2018(ኢዜአ)፡- የመደመር መንግሥት መፅሐፍ ፈጠራና ፍጥነት ወደ ተሻለ እመርታ ለመሸጋገር ቁልፍ መንገዶች መሆናቸውን ለአምራች ኢንዱስትሪው ያሳየ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ።

የኢንዱስትሪ ልማቱ ዘመኑን የዋጀና በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራር ተግባራዊ እንዲያደርግ የመደመር እሳቤ ጉልህ ሚና አበርክቷል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመደመር ዙሪያ የጻፉት ''የመደመር መንግሥት" 4ተኛ መፅሐፍ ሆኖ ለንባብ መብቃቱ ይታወቃል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል የመደመር መንግሥት መፅሐፍ ለኢንዱስትሪ ምርታማነት መጨመር ያለውን አንድምታ በሚመለከት ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

የመደመር መንግሥት ለአምራች ዘርፉ ትልቅ ትኩረት የሰጠ መሆኑን አብራርተዋል።

መፅሐፉ ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ያላትን ፍላጎት፣ የአምራች ኢንዱስትሪ ልማትን በስፋት ቀድመው የጀመሩ ሀገራት ተሞክሮን ጨምሮ አሁናዊ ሁኔታውን በዝርዝር አስቀምጧል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ያለባትን መዋቅራዊና የሃብት አጠቃቀም ችግር፣ የግብዓት፣ የሰው ኃይልና በኢንዱስትሪ ዘርፉ የሚስተዋለውን የቴክኖሎጂ ውስንነት በሚመለከት ሰፊ ትንታኔ መስጠቱንም ገልጸዋል።

ያሉ ክፍተቶችን መነሻ በማድረግ መፍትሔዎችን ጭምር ያመላከተ በመሆኑ የዘርፉን የአሰራር ስርዓት በምክንያታዊነት ለመፈተሽና በግብዓትነት ለመጠቀም እድል ፈጥሯል ነው ያሉት።

የመደመር መንግሥት ፈጠራና ፍጥነት የድህነት መውጫ ቁልፍ አድርጎ ማቅረቡን ጠቅሰው፥ በማምረት ውስጥ የሚገኝ ስኬትን የሚያጎላ ስለመሆኑም አብራርተዋል።

በመሆኑም ዘርፉን ወደ ተሻለ እመርታ ለማሸጋገር መፅሐፉ ትልቅ የእድገት ሰነድ ተደርጎ ይወሰዳል ብለዋል።

መንግሥት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረትና የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም አምራቾች ከመንግሥት ጋር ያላቸውን ትብብር በማጠናከር ቀጣይነት ያለው እድገት ለማስመዝገብ በቁርጠኝነት ሊሠሩ እንደሚገባ ገልጸዋል።

በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻየው የተከናወኑ ተግባራት፣ ለኢንዱስትሪ ምርታማነት መጨመር የተደረጉ የፖሊሲ ማሻሻያዎች ቀጣይነት ላለው እድገት እድል መፍጠራቸውን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም መንግሥት ለኢንዱስትሪ ዘርፉ ምርታማነት በመሰረተ ልማት አቅርቦት ላይ ተግባራዊ ያደረገው የአሠራር ስርዓት ዘርፉን ተወዳዳሪ ለማድረግ አስችሏል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን ተመራጭነትን የሚያሳድጉ ተግባራት መከናወናቸው እና አዳዲስ ሜጋ ፕሮጀክቶች መጀመራቸው አዲስ የልማት ምዕራፍ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም