በአሪ ዞን በክረምት ወራት የተተከሉ ችግኞችን ለውጤት ለማብቃት እንክብካቤ እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአሪ ዞን በክረምት ወራት የተተከሉ ችግኞችን ለውጤት ለማብቃት እንክብካቤ እየተደረገ ነው

ጂንካ፤መስከረም 28/2018(ኢዜአ) :-በአሪ ዞን በክረምት ወራት የተተከሉ ዘርፈ ብዙ ጠቃሜታ ያላቸው ሀገር በቀል ችግኞችን ለውጤት ለማብቃት ሕብረተሰቡን ያሳተፈ እንክብካቤ እየተደረገ መሆኑን የዞኑ ደንና አካባቢ ጥበቃ ልማት ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
በጽሕፈት ቤቱ የደን ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ቡድን መሪ አቶ ክንዴ ፍስሃ፤ በዞኑ የተራቆቱ አካባቢዎችን በማልማት የብዝሃ ሕይወት ጥበቃ ስራውን ለማጠናከር ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በክረምቱ ወቅት አርሶ አደሮችና ወጣቶችን ጨምሮ ከ174 ሺህ በላይ የሚሆኑ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር መካሄዱን አስታውሰዋል።
በመርሃ ግብሩ የአንድ ጀምበርን ጨምሮ ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው በርካታ ሀገር በቀል ችግኞች መተከላቸውን አንስተው፤ አሁን ላይ የተተከሉ ችግኞች እንዲጸድቁ የእንክብካቤ ስራ በየደረጃው እየተሰራ ነው ብለዋል።
ችግኞቹ በወቅቱ የተተከሉት በተራሮች አካባቢዎች መሆኑን ጠቅሰው፤ 1 ሺህ 421 ሄክታር መሬት ላይ የተፋሰስ ልማትና ሌሎች የብዝሃ ሕይወት ጥበቃ ስራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል።
በዞኑ ደቡብ አሪ ወረዳ የሸጲ ቀበሌ አርሶ አደር ማርቆስ ደጉ፥ በአካባቢው ቀደም ሲል የእርሻ ማሳ ለማስፋፋት ደኖች ያለ አግባብ ሲጨፈጨፉ እንደነበር አስታውሰዋል።
በአካባቢው የደኖች ያለ አግባብ መጨፍጨፍ የጎርፍና የአፈር መንሸራተት አደጋዎች እንዲከሰቱ ማድረጉን ጠቅሰው፥ይህም በግንዛቤ እጥረት እንደሆነ መረዳታቸውን ተናግረዋል።
አሁን ላይ ከግብርና ባለሙያዎች ባገኙት ግንዛቤ የተራቆቱ አካባቢዎችን እያለሙ የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን ገልጸዋል።
ባለፈው ክረምትም በህዝብ ተሳትፎ የተተከሉ ችግኞችን እየተንከባከብን ነው ያሉት አርሶ አደር ማርቆስ፤ ይህም ለአካባቢ ልማት እያስገኘ ያለውን ውጤት እየተመለከትን ስለሆነ የበለጠ ለማስፋት እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።
በዞኑ ባካ ዳውላ አሪ ወረዳ የሴኔጋል ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አለሙ ፈለቀ በበኩላቸው፤ በአካባቢው የአረንጓዴ ልማት ስራን ማከናወን ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ በጎርፍ የሚታጠበውን ለም መሬት መጠበቅ መቻላቸውን ገልጸዋል።