በሃይማኖታዊ እና ህዝባዊ በዓላት ላይ የታየው ህብረት ሌሎች ስራዎችን በውጤታማነት ለመከወን መሰረት የሚጥል ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
በሃይማኖታዊ እና ህዝባዊ በዓላት ላይ የታየው ህብረት ሌሎች ስራዎችን በውጤታማነት ለመከወን መሰረት የሚጥል ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 28/2018(ኢዜአ)፡- በሃይማኖታዊ እና ህዝባዊ በዓላት ላይ የታየው ህብረት ሌሎች ስራዎችን በውጤታማነት ለመከወን መሰረት የሚጥል ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያውያን አብሮነት እና ወንድማማችነት እሴት እየዳበረ መምጣቱንም ገልጸዋል፡፡
በአዲስ አበባ መስቀልና ኢሬቻን ጨምሮ በአደባባይ የተከበሩ በዓላት ስኬታማ ሆነው እንዲጠናቀቁ አስተዋጽኦ ላደረጉ ባለድርሻ አካላት የምስጋና መርሀ ግብር ተካሂዷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የመዲናዋ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ አባገዳዎች እና ሀደ ሲንቄዎችን ጨምሮ የጸጥታው ዘርፍ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
ከንቲባ አዳነች በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በመዲናዋ ከጳጉሜን ወር ጀምሮ በተከታታይ ሃይማኖታዊ እና ህዝባዊ በዓላት በስኬት ተከብረዋል፡፡
የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ፣ የአፍሪካና ካረቢያን ስብሰባን ጨምሮ ከ25 ሺህ በላይ እንግዶች የተሳተፉበት ትልልቅ ጉባኤዎች መካሄዳቸውንም አስታውሰዋል።
ሃይማኖታዊ እና የአደባባይ በዓላት ያለምንም የጸጥታ ችግር መካሄዳቸውን ገልጸው የሕዝቡ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ አመራሩ እና የጸጥታ መዋቅሩ በተቀናጀ እና በተናበበ መልኩ መስራታቸው ለተገኘው ውጤት ምክንያት መሆኑን አብራርተዋል።
ውጤቱ ለሀገራችን ትልቅ ትርጉም አለው ያሉት ከንቲባ አዳነች ይህም የህዝቡ እንግዳ ተቀባይነት፣ የወንድማማችነትና እህትማማችነት እንዲሁም የመከባበር እሴት እየዳበረ ለመምጣቱ ማሳያ ነው ብለዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በጋራ በመቆም አሳክተናል ያሉት ከንቲባ አዳነች የተፈጥሮ ጋዝና የነዳጅ ፕሮጀክትን ጨምሮ ትልልቅ ሀገራዊ የልማት ውጥኖች ከዳር ለማድረስ ህብረትና አንድነትን ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።
በሃይማኖታዊና ህዝባዊ በዓላት የታየው ህብረትና ትብብር ሌሎች የልማት ሥራዎችን በውጤታማነት መከወን እንደሚቻል ትምህርት የሰጠ ነው ሲሉም ተናግረዋል።