ኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድ የባህር በር የማግኘት ተፈጥሯዊ መብቷን እንድታሳካ ሚናችንን እንወጣለን-የምክር ቤት አባላት - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድ የባህር በር የማግኘት ተፈጥሯዊ መብቷን እንድታሳካ ሚናችንን እንወጣለን-የምክር ቤት አባላት
አዲስ አበባ፤ መስከረም 28/2018 (ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ህጎችንና ተፈጥሯዊ መብቷን ተጠቅማ የባህር በር ተጠቃሚ እንድትሆን ሚናችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለጹ፡፡
የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በ6ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ባሰሙት ንግግር ኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነቷን ከኩስመና ወደ ተለወጠ ቁመና በማሸጋገር ከማህጸኗ በፈለቁ ወንዞች ፍትሐዊ ተጠቃሚ መሆን መጀመሯን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝና ቀይ ባህር መካከል የምትገኝ ብትሆንም ከሁሉቱም ውሃዎች በኢ-ፍትሐዊነት ተገልላ የቅርብ ሩቅ ሆና መቆየቷን አንስተው፤ አስተማማኝ የባህር በር እንደሚያስፈልጋት ተናግረዋል፡፡
በዓባይ ወንዝ እና በቀይ ባህር ዙሪያ በተደረገው ያልተቋረጠ ጥረት ሕዳሴ ግድብን ከቀውስ በመታደግ ማጠናቀቅ፣ የባህር በር የማግኘት ተፈጥሯዊ መብታችንን በጎረቤትና በዓለም ሀገራት ዘንድ ቅቡልነት እንዲያገኝ ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡
በቀጣይም በሁለቱ ውኃዎች ላይ የኢትዮጵያ የመልማት ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ ትስስርና ትብብር ለመፍጠር ሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ከባህር በር ርቃ የቆየችበት መንገድ ተገቢ አልነበረም፡፡
በኢትዮጵያ የቀይ ባህርን ያጣችበት ሁኔታ የሚያስቆጭ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የምክር ቤቱ አባል ከፈና ኤፋ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የባህር በር ተጠቃሚነትን በሰጥቶ መቀበል መርህ አልያም በዓለም አቀፍ ህግ ማረጋገጥ አለባት ብለዋል፡፡
የባህር በር የህልውና ጉዳይ ነው ያሉት ከፈና (ዶ/ር) በኢ-ፍትሐዊ መንገድ የተነጠቅነውን የባህር በር በፍትሐዊ አካሄድ መልሰን ማግኘት ይገባናል ነው ያሉት፡፡
ሌላው የምክር ቤት አባል አጉ ደባን ኢትዮጵያ የባህር በር ተጠቃሚነቷን ለማረጋገጥ በሁለትዮሽና በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ጥረት እያደረገች መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በጋራ ተጠቃሚ በምንሆንበት አግባብ በሰላማዊ መንገድ ማግኘት ይገባናል ብለዋል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ተስፋዬ ባንጉ ኢትዮጵያ የባህር በር ተጠቃሚ መሆን የምትፈልገው በሰላማዊ መንገድ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በጋራ የመልማት ፍላጎት እንዳላት ገልጸው፤ ለዚህ ስኬት ደግሞ ምክር ቤቱ ህግ በማውጣትም ሆነ በውክልና ስራዎች ግንዛቤ በመፍጠር የበኩሉን ሚና ይወጣል ብለዋል፡፡
ሌላው የምክር ቤት አባል ረዳት ፕሮፌሰር ገነነ ገረቡ፤ ኢትዮጵያ በፍጥነት የሚያድግ ኢኮኖሚና ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር እያላት ከባህር በር መታገዷ ተገቢ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ህጎችም ሆነ በተፈጥሯዊ መብቷ የባህር በር ማግኘት እንዳለባት ገልጸው፤ አጀንዳው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እያገኘ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የባህር በር በውይይትና በሰጥቶ መቀበል መርህ በሰላማዊ መንገድ ልናገኝ ይገባል ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር ገነነ፤ ትውልዱም አጀንዳው አድርጎ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡