ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታን አጎልብቶ ለማስቀጠል የመደመር መንግስት መጽሐፍ ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታል- ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታን አጎልብቶ ለማስቀጠል የመደመር መንግስት መጽሐፍ ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታል- ምሁራን

ሆሳዕና ፤ መስከረም 28/2018(ኢዜአ)፡- ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታን አጎልብቶ ለማስቀጠልና ሁለንተናዊ እድገትን ለማፋጠን የመደመር መንግስት መጽሐፍ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት በዋቸሞ ዩኒቨርስቲ ምሁራን ገለጹ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተጻፈው ''የመደመር መንግሥት'' የተሰኘው መጽሀፍ ተመርቆ ለንባብ መብቃቱ ይታወሳል፡፡
በመጽሐፉ ዙሪያ ኢዜአ ያነጋገራቸው የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን እንዳመለከቱት፤ መጽሃፉ ያለፈውን ከመጪው ዘመን ጋር ያዋሀደ ጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታን ለመፍጠር የሚደረግ ጥረትን የሚያሳይ ነው፡፡
በዩኒቨርሲቲው የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት መምህር አስራት ኤርሞሎ፤ የመደመር መንግሥት መፅሐፍ ሀገር በቀል እዉቀትን መሰረት አድርጎ የሀገሪቱን ባሕልና እሴትን በጠበቀ መልኩ እንደተዘጋጀ መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ከነበሩ የተለያዩ የመንግሥት ስርዓቶች መልካም እሴቶችን በተሞክሮነት በመዉሰድ ለሀገረ መንግሥት ግንባታዉ መጠናከር እና መጠቀም ከዚህ ቀደም እንዳልታዩ አስታውሰው፤ መልካምን እሴት ባሕል አደርጎ ማስቀጠል ተገቢ መሆኑ አስረድተዋል፡፡
የመደመር መንግሥት መጽሐፍ ፍልስፍና መልካሙን እሴት ጠብቆ ጠንካራ የሀገረ መንግሥት ግንባታን አጎልብቶ ለማስቀጠል ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል ።
መጽሀፉ ሀገራዊ አንድነትን ከማጠናከር በተጨማሪ ለቀጣናዉ ትስስር፣ሰላም፣ለጋራ እድገትና ብልፅግና መረጋገጥ ጭምር ጉልህ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚገባም ያሳየ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ያለንን የተፈጥሮ ሀብቶች በአግባቡ በመጠቀም ኢንቨስትመትን መሳብና ማበረታታት እንዲሁም ሀገሪቱ የውጭ ባለሀብቶችን በመሳብ ማዕከል እንድትሆን በማድረግ የኢኮኖሚ ዕድገትን ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ ማፍጠን የሚያስችሉ ሀሳቦች የያዘ መሆኑን መመልከታቸውን ገልጸዋል፡፡
ሌላኛዉ በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት መምህር አቶ አበራ ሄቢሶ በበኩላቸው፤ የመደመር መንግሥት መጽሀፍ የሀገራችንን የዘመናት ቆይታንና ያልተመጣጠነ እድገትን በቁጭት ያመላከት ነው ብለዋል፡፡
ለሀገርና ለዜጎች ሁለንተናዊ እድገትና ተጠቃሚነት መረጋገጥ በጊዜ የለንም መንፈስ መስራት እንደሚገባ የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ በማመላከት ትምህርት የሚሰጥ መጽሐፍ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለአብሮነታችን ቅድሚያ በመስጠት ከዚህ ቀደም በተለያያ ምክንያቶች የባከኑብንን ጊዜያት ለአንድ ዓላማ በመሰለፍ መካስ እንደሚገባንና በዚህም መጪው ትውልድን ታሳቢ ያደረገ ስራ ለማከናወን በርካታ እድሎች መኖራቸውን ያሳየ ነው ያሉት፡፡
ከሁሉ በላይ የኢትዮጵያዊነት እሴት ጎልቶ እንዲወጣ በማድረግና የሀሳብ ልዕልናን በማስቀደምና በመትጋት ስኬቶችን ከወዲሁ ማምጣት እንደሚቻል ያመላከተ መጽሐፍ ስለመሆኑ ጠቅሰዋል፡፡
ለሀገራችን ብልፅግና መረጋገጥ በጋራ እንድንተጋ ጭምር አቅጣጫ የሚያመላክት ከመሆኑም ባለፈ አብሮነትና አንድነት ውስጥ ያለውን ሀይል በማቀናጀት መልማትና ማደግ እንደሚቻል ብሩህ ተስፋን የሰነቀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በመጽሀፉ የተቀመጡ ዕውነታዎች ወደ ተግባር እንዲለወጡ ከማንበብ ባሻገር በጊዜ የለንም መንፈስ ተግቶ መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡