ቀጥታ፡

መንግሥት ኢትዮጵያ መቀየር እና መበልጸግ አለባት ብሎ በቁርጠኝነት እየተጋ ይገኛል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ መስከረም 28/2018 (ኢዜአ)፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መንግሥት ኢትዮጵያ መቀየር እና መበልጸግ አለባት ብሎ በቁርጠኝነት አምኖ እየተጋ ይገኛል ሲሉ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት 7ኛው የታማኝ ግብር ከፋይ ዕውቅና እና ሽልማት ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል።

በዚሁ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ንግግር፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ኢትዮጵያ መቀየር አለባት፣ መበልጸግ አለባት ብሎ በቁርጠኝነት አምኖ እየተጋ ይገኛል ሲሉ አስገንዝበዋል።

ይህ ትጋቱ ሊሳካ የሚችለውም እንደ እናንተ ባሉ ታማኝ የሥራ ፈጣሪዎች፣ ግብር ከፋዮች፣ ሠሪዎች እና አሠሪዎች መሆኑን በጽኑ እናምናለን ብለዋል።

በዚሁ አግባብ በመንግሥትና በታማኝ ግብር ከፋዮች መካከል በጥቂት ጉዳዮች ላይ በጽሑፍ ያልሆነ ስምምነት እንድንፈጽም እፈልጋለሁ ነው ያሉት።

በዚህም መሠረት አንደኛ፣ በእናንተ በኩል የግሉ ሴክተር ከትርፍ በላይ ማኅበራዊ ዓላማን ያነገበ ሥራ የእያንዳንዱ ኩባንያ የሥራ ኃላፊዎች እና ባለቤቶች አንዱ ዋነኛ ተልዕኮ መሆን እንዳለበት አስረድተዋል።

ሠርቶ ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ ግብር የሚከፍል ሰው ከትርፍ በላይ ለማኅበራዊ ዓላማ ራሱን ማዘጋጀት ይኖርበታል ሲሉም ጠቁመዋል።

ሁለተኛ፤ በእኛ በኩል በታማኝነት ልናገለግላችሁ ስለወሰንን በስኬትም ሆነ በተግዳሮት ከመንግሥትና ከሕዝብ ጋር የምትጋሩ ታማኞች መሆን አለባችሁም ነው ያሉት።

በደኅናው ዘመን የምትሰበስቡና ሐብት የምታካብቱ በችግር ጊዜ ደግሞ ወደ ዱባይ የምትሸሹ መሆን የለባችሁም፤ በመከራውም ሆነ በስኬቱ ጊዜ በጋራ ጸንተን የምንቆም መሆን አለብን ሲሉም በአጽንኦት ገልጸዋል።

ሦስተኛ፤ የሀገርን ጥቅም እና ትውልድን የምታስቀድሙ መሆን አለባችሁ ነው ያሉት።

የምንሠራው ለእኛ ብቻ ሳይሆን፤ ለትውልድ ጭምር ነው የሚለውን አምናችሁ እና ከልብ ተቀብላችሁ የምትተገብሩ መሆን ይጠበቅባችኋል ሲሉም አስገንዝበዋል።

ይህ ሲሆን ከሰፈሮቻችን ወጥተን ላቅ ያለ ሥራ ለመሥራት በእጅጉ ያግዘናል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም