የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ ለማሳካት ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚያጎለብቱ ተግባራት ትኩረት ተሰቷቸዋል- አቶ አገኘሁ ተሻገር - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ ለማሳካት ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚያጎለብቱ ተግባራት ትኩረት ተሰቷቸዋል- አቶ አገኘሁ ተሻገር

አዲስ አበባ፤ መስከረም 28/2018 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ ለማሳካት ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚያጎለብቱ ተግባራት ትኩረት እንደተሰጣቸው የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት በ6ኛ የፓርላማ ዘመን 5ኛ ዓመት የሥራ ጊዜ 1ኛ መደበኛ ስብሰባ የመንግስታት ግንኙነት፣ ዴሞክራሲያዊ አንድነትና የሕገ-መንግስት አስተምህሮ ቋሚ ኮሚቴ እንዲሁም የሕገ መንግስትና የፌደራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል የ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸምን በማዳመጥ የ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ተወያይቶ አጽድቋል።
በፌዴሬሽን ምክር ቤት የመንግሥታት ግንኙነት፣ የዴሞክራሲያዊ አንድነትና የሕገ መንግሥት አስተምህሮ ቋሚ ከሚቴ ጸሐፊ ወይዘሮ ባንችይርጋ መለሰ÷ 19ኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ሕብረብሔራዊ አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ በአርባ ምንጭ ከተማ በድምቀት መከበሩን አስታውሰዋል።
በቀጣይም የፌደራል ሥርዓቱ ጤናማነቱ የተረጋገጠና ተቋማዊነቱ የተጠናከረ እንዲሆን የሚያስቸል ድጋፍና ክትትል ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
በሕገ-መንግስትና ፌደራሊዝም ዙሪያ የዜጎችን ግንዛቤ በማሳደግ ብሔራዊ መግባባትና የህዝቦችን አንድነት የሚያጎለብቱ የአስተምህሮ ስርጸት ተግባራት ትኩረት እንደሚሰጣቸው አስረድተዋል።
20ኛው የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ብዝኃነት ላይ የተመሰረተ ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን በሚያጎላ መልኩ በድምቀት ማክበር የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።
ክብረ በዓሉ የህዝቦችን የነቃ ተሳትፎ ባረጋገጠ መልኩ በሁሉም ክልሎችና ከተማ መስተዳደሮች በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበርና በሀገር አቀፍ ደረጃ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ እንደሚከበር አስተረድተዋል።
በፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ መንግስትና የፌደራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ኃይለ ኢየሱስ ታዬ (ዶ/ር)÷ ባለፈው ዓመት በትምህርት ተቋማትና በመገናኛ ብዙኃን የፌደራሊዝም አስተምህሮ ተግባራት መከናወኑን ገልጸዋል።
በተያዘው በጀት ዓመትም በጥናትና ምርምር፣ በፌደራሊዝምና ሕገ-መንግስታዊ አስተምህሮ የዜጎችን ግንዛቤ የሚያሳድጉ ተግባራት እንደሚከናወኑ አስገንዝበዋል።
የምክር ቤቱ አባል ወንዳለ ሀብታሙ (ዶ/ር)÷ በመንግስታት ግንኙነት፣ በሕገ መንግስትና የፌደራሊዝም አስተምህሮ የዜጎችን ህብረ ብሔራዊ አንድነት የሚያስጠብቁ ተግባራት መጠናከር ይኖርባቸዋል ብለዋል።
የዜጎችን አንድነት ለማጠናከርም በሕገ መንግስትና ፌደራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል በኩል ኪነ-ጥበብንና የትምህርት ሥርዓቱን በመጠቀም ግንዛቤን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር በማጠቃለያቸው÷ ኢትዮጵያ በማንሰራራት ዘመን ጉዞ ላይ ናት ብለዋል።
የዜጎችን ሕብረ ብሔራዊ መግባባትና አንድነት የሚያጎለብቱ የአስተምህሮና የስርጸት ተግባራት በትኩረት እንደሚሰራባቸው አንስተዋል።
20ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ታላላቅ ሀገራዊ አጀንዳዎች በሚከወኑበት ወቅት የሚከበር በመሆኑ ልዩ ትርጉም እንደሚሰጠው ተናግረዋል።
በዓሉ ህብረ ብሔራዊነትን በማጎልበት የሀገርን የማንሰራራት ጉዞ በሚያሳካ መልኩ በልዩ ድምቀት እንደሚከበር ጠቅሰዋል።