የባሌ ዞን አርሶ አደሮች በመኸሩ ወቅት በኩታ ገጠም ካለሙት የስንዴ ሰብል የተሻለ ምርት ለማግኘት የሰብል ጥበቃ እና እንክብካቤ አጠናክረዋል - ኢዜአ አማርኛ
የባሌ ዞን አርሶ አደሮች በመኸሩ ወቅት በኩታ ገጠም ካለሙት የስንዴ ሰብል የተሻለ ምርት ለማግኘት የሰብል ጥበቃ እና እንክብካቤ አጠናክረዋል
ሮቤ፤ መስከረም 28/2018 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል የባሌ ዞን አርሶ አደሮች በመኸሩ ወቅት በኩታ ገጠም ካለሙት የስንዴ ሰብል የተሻለ ምርት ለማግኘት የሰብል ጥበቃ እና እንክብካቤ ማጠናከራቸውን ገለጹ።
በዞኑ በ2017/18 የመኽር ወቅት በተለያዩ የሰብል ዘሮች የለማው ከ528 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት እንክብካቤ እየተደረገለት መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገልጿል።
ለኢዜአ አስተያየታቸውን ከሰጡት የዞኑ አርሶ አደሮች መካከል አቶ ጫላ ደሙ እንዳሉት ግብዓትን በአግባቡ ለመጠቀምና ምርታማነትን ለማሳደግ የኩታ ገጠም እርሻ ጥቅሙ የጎላ ነው።
በተለይም ሰብልን በኩታ ገጠም ማልማት ከጀመሩ ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ ምርታማነታቸው እየተሻሻለ በመምጣቱ ከአንድ ሄክታር የስንዴ ማሳ የተሻለ ምርት ማግኘት መጀመራቸውን አስታውሰዋል።
በመኸሩ ወቅት ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር በኩታ ገጠም አሰራር አምስት ሄክታር መሬት ስንዴ በማልማት አረም እያረሙ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ አርሶ አደር ጣፋ ኤጄሬ ናቸው።
አረምን በወቅቱ ማንሳታቸው የስንዴ ሰብሉ በጥሩ ቁመና ላይ እንዲገኝ ስለሚያደርግ ከአንድ ሄክታር ስንዴ እስከ 75 ኩንታል ምርት እንደሚጠብቁ አስታውቀዋል።
አርሶ አደር ከድር አህመድ በበኩላቸው ከምርምር ማዕከላት የተገኙ ምርጥ ዝርያ የአረምና በሽታ ቁጥጥር በወቅቱ በማከናወን ከአንድ ሄክታር እስከ 65 ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ተግተው እየሰሩ መሆናቸውን አመልክተዋል ።
የአጋርፋ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተገኔ ቶሎሳ በበኩላቸው በወረዳው በመኸሩ ወቅት በተለያዩ የሰብል ዘሮች የለማው ከ76 ሺህ 700 ሄክታር የሚበልጥ መሬት በአርሶ አደሩ እንክብካቤ እየተደረገለት ነው።
ከለማው አጠቃላይ መሬትም 46 ሺህ ሄክታር የሚበልጠው መሬት የተሻሻሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችና አሰራሮችን በመጠቀም በኩታ ገጠም የለማ ስንዴ እንደሆነ ተናግረዋል።
የባሌ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ሙኣዊያ ፉአድ በበኩላቸው እንዳሉት በዞኑ በመኸሩ የምርት ወቅት ከ528 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት በተለያዩ የሰብል ዘሮች ለምቷል።
በተለይም በምርት ዘመኑ ስንዴን ጨምሮ ሌሎች የተመረጡና ምርታማ የሆኑ የሰብል አይነቶች በኢንሼቲቭ መልኩ በኩታ ገጠም እየለሙ መሆናቸውን አክለዋል።
በዞኑ በዘንድሮ የመኸር ወቅት የዝናብ ስርጭቱ የተስተካከለ በመሆኑ ከ19 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅም ምክትል ኃላፊው አስታውቀዋል።