ኢትዮጵያ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከጊኒ ቢሳው ጋር ትጫወታለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከጊኒ ቢሳው ጋር ትጫወታለች

አዲስ አበባ፤ መስከረም 28/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከጊኒ ቢሳው ጋር ዛሬ ጨዋታዋን ታደርጋለች።
የሁለቱ ሀገራት ጨዋታ ከቀኑ 10 ሰዓት በሩዋንዳ አማሆሮ ስታዲየም ይካሄዳል።
በምድብ አንድ የምትገኘው ኢትዮጵያ በስድስት ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
በአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እስከ አሁን በምድቡ ባደረጋቸው ስምንት ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ አራት ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪ ሶስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል።
ዋልያዎቹ ከዓለም ዋንጫ ውድድር ውጪ መሆናቸው ይታወቃል።
በአሚሊያኖ ቴ የምትመራው ጊኒ ቢሳው በ10 ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። በስምንት ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ ስታሸንፍ በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ ተሸንፋለች። አራት ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይታለች። ቡድኑ ከዓለም ዋንጫ ውጭ መሆኑ የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከጊኒ ቢሳው ጋር ላለበት ጨዋታ በሀገር ቤት ዝግጅቱን ሲያደርግ ቆይቶ ማክሰኞ መስከረም 27 ቀን 2018 ዓ.ም ወደ ሩዋንዳ ማምራቱ ይታወቃል።
ብሄራዊ ቡድኑ ለጨዋታው የመጨረሻው ልምምዱን ትናንት ማምሻውን በአማሆሮ ስታዲየም የልምምድ ሜዳ ማከናወኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
ሁለቱ ቡድኖች በምድቡ ባደረጉት የመጀመሪያ የማጣሪያ ጨዋታ ያለ ምንም ግብ አቻ መለያየታቸው የሚታወስ ነው።
ኢትዮጵያ የዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዋን ጥቅምት 2 ቀን 2018 ዓ.ም ኦጋዶጉ ላይ ከቡርኪናፋሶ ጋር ታደርጋለች።
ምድብ አንድን ግብጽ በ20 ነጥብ ስትመራ ቡርኪናፋሶ በ15 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ትከተላለች።
በዚሁ ምድብ ግብጽ ከጅቡቲ፣ ቡርኪናፋሶ ከሴራሊዮን ዛሬ በተመሳሳይ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።