የታላቁ የህዳሴ ግድብ ስኬት ኢትዮጵያውያን ከተባበርን የኢትዮጵያን ብልጽግና ማረጋገጥ እንደሚቻል የሚያሳይ ነው-ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የታላቁ የህዳሴ ግድብ ስኬት ኢትዮጵያውያን ከተባበርን የኢትዮጵያን ብልጽግና ማረጋገጥ እንደሚቻል የሚያሳይ ነው-ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤መስከረም 27/2018 (ኢዜአ)፡-ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን ከተባበርን የኢትዮጵያን ብልጽግና በአጭር ጊዜ ውስጥ ማረጋገጥ እንደሚቻል የሚያሳይ ነው ሲሉ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ገለጹ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅን አስመልክቶ የተቋሙ ሠራተኞች፣ባለድርሻ አካላት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት የምስጋና መርሃ ግብር እያካሄደ ነው።
በምስጋና መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ(ዶ/ር) እንደገለጹት፤ግድቡ በዛሬው እለት እውቅና የተሰጣቸው ተቋማትና ግለሰቦች ብቻ ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያውያን ተሳትፎ ያለበት ነው ብለዋል።
ግድቡ ጅማሮ እንጂ መጨረሻ አይደለም ያሉት ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያን ለማበልጸግ ትውልዱ መረባረብ አለበት ብለዋል።
የአሁኑ ትውልድ የዘመናት የህዝብ ቁጭትን ወደ ተግባር በመቀየር የኢትዮጵያን ከፍታ እያረጋገጠ ይገኛል ነው ያሉት።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን ከተባበርን የኢትዮጵያን ብልጽግና በአጭር ጊዜ ውስጥ ማረጋገጥ እንደሚቻል የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመው፤ ድሉ በሌሎች ፕሮጀክቶችም ሊደገም ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ በበኩላቸው፤ ግድቡ በርካታ ውስብስብ ችግሮችን አልፎ በለውጡ መንግስት ቆራጥ አመራር ግንባታው ተጠናቆ ለምርቃት መብቃቱንም ጠቅሰዋል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ የሀገሪቱን የሀይል የማመንጨት አቅም 10 ሺህ ሜጋ ዋት ማድረሱን ገልጸዋል፡፡
በዚህም የሀይል አቅርቦት ተደራሸነትን ከ54 በመቶ ወደ 78 በመቶ ለማድረሰ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ድርሻው የጎላ ነው ብለዋል።
ታላቁ የህዳሴ ግድብ የትውልዱ የአንድነት፤ የአይበገሬነት ማሳያና የአገሪቱ የማንሰራራት ጉዞ ጅማሬ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የሀይል ፍጆታ ከማሟላት ባለፈ ለአፍሪካ የሀይል አቅርቦትና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ትልቅ አቅም መሆኑን ገልጸዋል።