በፌደራል መንግስት የሚገነቡ መሰረተ ልማቶችን ፍትሐዊነት ለማረጋገጥ ጥብቅ ክትትል እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በፌደራል መንግስት የሚገነቡ መሰረተ ልማቶችን ፍትሐዊነት ለማረጋገጥ ጥብቅ ክትትል እየተደረገ ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 27/2018 (ኢዜአ)፦ በፌደራል መንግስት ባለቤትነት የሚገነቡ የመሠረተ ልማት አውታሮችን ሥርጭት ፍትሐዊነት ለማረጋገጥ ጥብቅ ክትትል እየተደረገ እንደሚገኝ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት የተለያዩ ቋሚ ኮሚቴዎችን የዕቅድ አፈፃጸምና የ2018 ዓ.ም ዕቅድ በ6ኛ የፓርላማ ዘመን 5ኛ ዓመት የሥራ ጊዜ 1ኛ መደበኛ ስብሰባ በተያዙ ስምንት አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ አጽድቋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር÷ የመረጃንና ማስረጃ የአሰራር ሥዓትን የተከተለ የፌደራል መንግስት የድጎማ በጀት ትልልፍ ሥርዓትን የማጠናከር ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የፌደሬሽን ምክር ቤት ፍትሐዊ የመሰረተ ልማት ሥርጭትን ለማረጋገጥ ጥብቅ ክትትል እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመው÷ ለዚህም የመሰረተ ልማት ስርጭት ፍትሐዊነት ማረጋገጫ መስፈርት በማውጣት እየተሰራበት እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
የበይነ መንግስታት የፊስካል ሽግግሮችን በፍትሐዊነትና ውጤታማነት ለማጠናከርም የቋሚ ኮሚቴ አባላት እያበረከቱት ያለውን ገንቢ ድጋፍ አጠናክረው መቀጠል እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል።
አዳዲስ ክልሎችም የህዝባቸውን የልማት ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት የሚያስመዘግቡትን እመርታዊ ስኬት አጠናክረው ማስቀጠል እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።
በፌዴሬሽን ምክር ቤት የድጎማ በጀትና የጋራ ገቢዎች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ጸሐፊ አቶ ኃይሉ ኢፋ ÷ የ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀምን እንደመነሻ በመውሰድ የ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት ዕቅድ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።
የበይነ መንግስታትን የፊስካል ሽግግር ፍትሕዊነትና ውጤታማ የማስፈጸም አቅም በማጎልበት የድጎማና የጋራ ገቢዎች አስተዳደርና የማካፈያ ቀመርን የመከታተልና የመደገፍ ስራ እንደሚከናወን ገልጸዋል።
የፌደራል የመሠረተ ልማት አውታሮች ሥርጭት ፍትሐዊነትና ውጤታማነት ክትትል አቅምን የማሳደግ ስራም በበጀት ዓመቱ ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በተለይም ልዩ ዓላማ ያላቸው የፌደራል ድጎማዎች በግልጽነት፣ ተጠያቂነትና ዘላቂ የአሰራር ሥርዓት ለክልሎች መከፋፈላቸውን የማረጋገጥ ስራ ጥብቅ ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
የመንግስታት ፊስካል ሽግግሮችን ፍትሐዊነትና ውጤታማነት በጋራ ገቢዎች አሰባሰብ፣ አስተዳደርና ትልልፍ ሂደት ጉልህ ስኬት እየተገኘበት መሆኑን አስረድተዋል።
ለአብነትም በ2012 በጀት ዓመት 4 ነጥብ 2 ቢሊየን የነበረው የክልሎች ድርሻ በ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት ወደ 91 ነጥብ 73 ቢሊዮን ብር ማደጉን አብራርተዋል።
በ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት የበይነ መንግስታትን ፊስካል ሽግግሮችን በፍትሐዊነትና በውጤታማነት በመምራት የፌደራል መሠረተ ልማት አውታሮች ክልላዊ ሥርጭት በተዘረጋው የአሰራር ሥርዓት መፈጸሙን ማረገገጥ የትኩረት መስክ መሆኑን አስረድተዋል።
የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው፤ የክልሎችን የዕድገት ደረጃ ተመጣጣኝነት ለማረጋገጥ እየተተገበረ ባለው አሰራር የፊስካል ሽግግሮች ፍትሐዊነትና ውጤታማነት ከፍተኛ ውጤት መምጣቱን ገልጸዋል።
በአዲስ መልክ ለተደራጁ ክልሎችም ለ2018 በጀት ዓመት የድጎማ በጀት ማከፋፈያ ቀመሩ ተግባራዊ የሚሆንበት ሥርዓት እንዲፈጠር ጠይቀዋል።
የፌደራል መሠረተ ልማት አውታሮች ክልላዊ ሥርጭትና በግንባታ ሂደት የሚስተዋሉ የአፈፃፀም ግድፈቶች ላይ በጥብቅ ድጋፍና ክትትል ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠይቀዋል።
በፌዴሬሽን ምክር ቤት የድጎማ በጀትና የጋራ ገቢዎች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ጸሐፊ አቶ ኃይሉ ኢፋ በምላሻቸው÷ ውስን ዓላማ ባላቸው የፌደራል መንግስት ድጎማዎች ትልልፍና ክትትል የተመዘገበው ውጤት ተጠናክሮ ቀጥላል ብለዋል።
የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እና በፌዴሬሽን ምክር ቤት የድጎማ በጀትና የጋራ ገቢዎች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ አሻድሊ ሀሰን÷ የጋራ ገቢና ለክልሎች የሚደረገው ትልልፍ ዕድገት እያስመዘገበ ነው ብለዋል።
አዳዲስ ክልሎችን ጨምሮ በሁሉም ክልሎች የአሰራር ሥርዓትን በተከተለ አግባብ ተመጣጣኝና ፍትሐዊ የመሠረተ ልማት ሥርጭትን ለመፍጠር በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
በ6ኛ የፓርላማ ዘመን 5ኛ ዓመት የሥራ ጊዜ 1ኛ መደበኛ ስብሰባው የፌዴሬሽን ምክር ቤት የ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት የድጎማ በጀትና የጋራ ገቢዎች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ዕቅድ በሙሉ ድምጽ ጽድቋል።
በመጨረሻም የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ የሕገ-መንግሥት ትርጉም ያስፈልጋቸዋል በማለት በ13 ጉዳዮች ላይ ያቀረባቸውን የውሳኔ ሃሳቦች መርምሮ ለምክር ቤቱ በማቅረብ አስጸድቋል።