ቀጥታ፡

በደሴ የሰፈነውን ሰላም በማስጠበቅ የልማት ስራው የበለጠ እንዲፋጠን ክትትልና ድጋፉ ይጠናከራል- ምክር ቤቱ

ደሴ፤ መስከረም 27/2018(ኢዜአ)፡- በደሴ  ከተማ የሰፈነውን ሰላም በማስጠበቅ የልማት ስራው የበለጠ እንዲፋጠን ክትትልና ድጋፉን  እንደሚያጠናክር የከተማ አስተዳደሩ  ምክር ቤት ገለጸ።

በከተማው የሚካሄዱ የደሴ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት 44ኛ መደበኛ ጉባኤ እየተካሄደ ነው።

የምክር ቤቱ ዋና አፈ ጉባዔ  አቶ አህመድ ሙህዬ  በጉባዔው መድረክ ባደረጉት ንግግር፤ በከተማው  የሰፈነውን ሰላምን በማፅናት  የልማት  ተግባራት እንዲፋጠኑ  ተገቢውን ክትትልና ድጋፍ ሲደረግ መቆየቱን  ገልጸዋል።


 

በዚህም በከተማው ሰላምን በማስጠበቅ በመሰረተ ልማት፣ በጽዳትና ውበት ጨምሮ በሌሎችም ዘርፎች  ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን በክትትል ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።

በከተማው ታይቶ የማይታወቅ ልማት እየተሰራ ነው ያሉት ደግሞ የምክር ቤት አባል ወይዘሮ ሰርካለም አበበ ናቸው።

ሕብረተሰቡ አንድነቱን በመጠበቅ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ፈጥነው እንዲጠናቀቁ ክትትልና ደጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል። 


 

ሌላው የምክር ቤቱ አባል አቶ ቴዎድሮስ አድማሴ፤ በከተማው በተለያዩ ዘርፎች እየተመዘገቡ ያሉ አበረታች ውጤቶች  እንዲቀጥሉ እያደረግን ያለውን ድጋፍና ክትትል  እናጠናክራለን ብለዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ በበኩላቸው፤ ሕብረተሰቡን በማስተባበር የከተማዋን ሰላም ከመጠበቅ ባለፈ ሰፋፊ የልማት ስራዎች ሲከናወኑ እንደቆዩ አውስተዋል። 


 

በዚህም በኮሪደር ልማት፣ በስራ እድል ፈጠራ፣ በገቢ አሰባሰብ፣ በመሰረተ ልማት፣ በመልካም አስተዳደርና ገበያ በማረጋጋት አበረታች ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።

የተጀመሩትን ፈጥኖ በማጠናቀቅና አዳዲስ የልማት ስራዎችን በማስጀመር የሕዝቡን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማጎልበት የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱም ለተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች አንድ ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ብር ተመድቦ ወደ ስራ መገባቱን ጠቁመው፤  የሕብረተሰቡን ተሳትፎና ትብብር በማከል ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ይሰራል ብለዋል።

ዛሬ ጨምሮ ለሁለት ቀናት በሚቆየው የምክር ቤቱ ጉባዔ  የምክር ቤቱ አባላትና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም