ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የ"ቃል ኪዳን ቤተሰብ"ን ለመተግበር ተግባራዊ እንቅስቃሴ ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የ"ቃል ኪዳን ቤተሰብ"ን ለመተግበር ተግባራዊ እንቅስቃሴ ጀመረ
ጋምቤላ ፤ መስከረም 27/ 2018 (ኢዜአ)፦ ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማሩን ተግባር ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ የሚያግዝ የ" ቃል ኪዳን ቤተሰብ"ን ለመተግበር ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታወቀ።
ዩኒቨርሲቲው ከጋምቤላ ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር ''የማህበራዊ ትስስራችን ለአብሮነታችን’’ በሚል መሪ ሃሳብ የ"ቃል ኪዳን ቤተሰብ "ማስጀማሪያ መርሃ ግብር ዛሬ አካሂዷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዲሪባ ኢቲቻ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ተቋሙ የተቀበላቸውን ተማሪዎች ከማስተማር ባለፈ የከተማው ነዋሪ አንድ ተማሪን በቃል ኪዳን ቤተሰብ በማስተሳሰር ድጋፍና እንክብካቤ እንዲያገኝ እያመቻቸ ነው።
የ"ቃል ኪዳን ቤተሰብ" ከሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ወደ ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲው የሚመጡ ተማሪዎችን ከከተማው ነዋሪዎች ጋር በማስተሳሰር እንግድነት ሳይሰማቸው ትምህርታቸው ላይ እንዲያተኩሩ የሚያደርግ አሰራር መሆኑን አስረድተዋል።
የ"ቃል ኪዳን ቤተሰብ" ቀደም ሲል በጎንደር የኒቨርሲቲ ተጀምሮ ለመማር ማስተማር ሂደትና ለትምህርት ጥራት አስተዋጽኦ በማበርከቱ ተሞክሮውን በመውሰድ ለመተግበር እንቅስቃሴ መጀመራቸውን አስታውቀዋል።
ይህም የመማር ማስተማር ስራውን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ከማገዝ ባለፈ አብሮነትን ይበልጥ የማጠናከር አቅም እንዳለው ተናግረዋል።
የጋምቤላ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ተወካይ አቶ ፓል ቱት በበኩላቸው፤ መርሀ ግብሩ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ወደ ዩኒቨርሲቲው የሚመጡ ተማሪዎች ከመደበኛ ትምህርታቸው በተጨማሪ አንድነትና አብሮነታቸውን እንዲያጠናክሩ ያግዛል ብለዋል።
ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው ቆይታቸው ከትምህርታቸው ጎን ለጎን ዩኒቨርሲቲው የተቋቋመበት አካባቢ ማሕበረሰብ ባሕልና ቋንቋ ይበልጥ በመረዳት ሕብረብሔራዊነት እንዲጎለብት የሚረዳ መሆኑን አንስተዋል።
የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች የመጡበትን ዓላማ በስኬት አጠናቀው እንዲመለሱ ከዩኒቨርሰቲው ጋር የጀመርነውን የድጋፍና ትብብር ስራ አጠናክረን እንቀጥላለን ያሉት ደግሞ የጋምቤላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ሳይመን ሙን (ዶ/ር) ናቸው።
በመርሃ ግብሩ ላይ የክልሉና የዩኒቨርሲቲው አመራሮችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።