ቀጥታ፡

የመንግስት የትኩረት አቅጣጫዎች የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡና የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ እውን የሚያደርጉ ናቸው

አዲስ አበባ፤መስከረም 27/2018 (ኢዜአ)፡-ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ለሁለቱ ምክር ቤቶች ያቀረቧቸው የዚህ ዓመት የመንግስት የትኩረት አቅጣጫዎች የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡና የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ እውን የሚያደርጉ መሆናቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

ስድስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አምስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን የጋራ ስብሰባ በትላንትናው እለት መካሄዱ ይታወቃል።

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ለሁለቱ ምክር ቤቶች በጋራ ስብሰባው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት የተከናወኑ ተግባራትን በማንሳት የቀጣይ የመንግስት የትኩረት አቅጣጫዎችን ይፋ አድርገዋል።

ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው፥ በዓባይና በቀይ ባሕር ላይ ያተኮሩ ዲፕሎማሲያዊና ሰላማዊ ጥረቶችን አጠናክሮ ማስቀጠል፣የዲጂታል አገልግሎትን ማስፋት፣ የዋጋ ንረትን መቆጣጠር፣ የቱሪዝም መስህቦችን ማዘመንና ማሳደግ፣ የትምህርትና የጤና ስርዓትን ማዘመንና ሌሎችም ጉዳዮች የመንግስት የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።

ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ባነሷቸው የመንግስት የትኩረት አቅጣጫዎች ዙሪያ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር አነጋግሯል።

አቶ ተዋበ ገድሌ እንደተናገሩት፣ የቀረቡት የመንግስት የትኩረት አቅጣጫዎች የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ናቸው።

በተለይ መንግስት በስርዓት ለውጥ የማይናወጡ ጠንካራ ተቋማትን ለመገንባትና የዜጎችን ህይወት ለማሻሻል የሰጠው ትኩረት የሚደነቅ ነው ብለዋል።

የቀጣይ አቅጣጫዎች ህዝብን ያነቃቁ እና የማንሰራራት ጉዞን እውን የሚያደርጉ በመሆናቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጭ አቶ በቀለ መንግስቱ በበኩላቸው፤ የቀረቡት አቅጣጨዎች መንግስት ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።

የተቀመጠው አቅጣጫ አገራችንን ከድህነት በማላቀቅ በምግብ ራስን ለመቻል እየተደረገ ላለው ርብርብ ትልቅ አቅም የሚሆን ነው ብለዋል።

አቶ አስማማው ደሞዝ በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት፤ መንግስት ሰላምን ለማረጋገጥ እያሳየ ያለው ፍላጎትና እየወሰዳቸው ያሉት እርምጃዎች የሚደገፉና የሚበረታቱ ናቸው ብለዋል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ አልዩ መሐመድ በበኩላቸው፥ የተቀመጡ አቅጣጫዎች በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎትን ተደራሽ በማድረግ የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም