ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ተወዳዳሪ የጤና ስርዓት ለመገንባት በትኩረት እየሰራች ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 27/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አልፎ በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ የጤና ዘርፍ ለመገንባት የሚያስችል ስርዓት ዘርግታ እየሰራች መሆኑን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንዱስትሪ እና የማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አማረች ባካሎ (ዶ/ር) ገለጹ።  

ይህ የተገለጸው በቂሊንጦ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን የሚገኘው ቅጥራን ማኑፋክቸሪንግ ሜዲካል ኢኮዩፕመንት ትሬዲንግ ተመርቆ ስራ በጀመረበት ወቅት ነው።  


 

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንዱስትሪ እና የማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አማረች ባካሎ (ዶ/ር) በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት፣ መንግስት ለአገር ብልጽግና መረጋገጥ በትኩረት እየሰራ ነው፡፡

ለዚህም ለግሉ ዘርፍ የላቀ ትኩረት በመስጠት በተለያዩ የልማት ዘርፎች እንዲሰማራ ሁለንተናዊ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።  

ከአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ መካከልም ለመድሃኒትና የህክምና መሳሪያዎች አምራቾች በርካታ ድጋፎችና ምቹ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል።  

ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ ተግባራት በጤናው ዘርፍ ለውጦች እየተመዘገቡ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ በጤናው ሴክተር ከአፍሪካ አልፎ በአለም ተወዳዳሪ ስርዓት ለመፍጠር በርካታ ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነች እንደምትገኝ አንስተው ሁሉም በትብብር እንዲሰራ ጥሪ አቅርበዋል።


 

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ፍሬሕይወት አበበ በበኩላቸው፤ የጤና ዘርፉን ጥራትና ፍትሓዊነት ለማረጋገጥ ባለፉት ዓመታት በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቅሰዋል። 

በተለይ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ትግበራን ተከትሎ በጤናው ዘርፍ ውጤታማ ተግባር መከናወን መቻሉን አንስተው፣ ሪፎርሙ በዘርፉ የሚገኙ የአገር ውስጥ አምራቾች እንዲበረታቱ ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ እንደሚገኝ አስረድተዋል። 

‎‎የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ፣ የቅጥራን ማኑፋክቸሪንግ ወደ ስራ መግባቱ ለኢትዮጵያ ትልቅ ብስራት መሆኑን ተናግረዋል። 


 

ተቋሙ በአገሪቱ ለሚገኙ የጤና ተቋማት የመድሃኒት አቅርቦት ከማሻሻል በተጨማሪ የውጭ ምንዛሬን በማስቀረት ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው አስታውቀዋል።


 

የቂሊንጦ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ስራ አስኪያጅ ቶሎሳ ባደዳ በበኩላቸው፤ ኢኮኖሚ ዞኑ ከፍተኛ መዋለ ንዋይ ፈሶበት የመድሃኒት ቁሳቁሶች እንዲመረቱበት የተቋቋመ መሆኑን አስታውሰዋል። 

የቅጥራን ማኑፋክቸሪንግ ሜዲካል ኢኮዩፕመንት ትሬዲንግ ካምፓኒ ወደ ስራ መግባቱ በቀጣይ ልዩ ኢኮኖሚ ዞኑ የያዘውን ራዕይ ለማሳካትና ሌሎች አምራቾች ወደ ልዩ ኢኮኖሚክ ዞኑ እንዲገቡ መንገድ የሚከፍት መሆኑን ተናግረዋል።


 

የቅጥራን ማኑፋክቸሪንግ ሜዲካል ኢኮዩፕመንት ትሬዲንግ ስራ አስኪያጅ አታኩሬ አያሌው እንዳሉት ቅጥራን ለዛሬው ቀን እንዲበቃ መንግስት ያደረገው ሁለንተናዊ ድጋፍ ከፍተኛ ሚና እንደነበረው አስታውሰው፤ በቀጣይም ውጤታማ ለመሆን በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም