ቀጥታ፡

Pulse of Africa በአፍሪካ ቀዳሚ የመሆን ህልሙ ፍሬያማ እንዲሆን በትጋት መስራት ይገባል-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ መስከረም 27/2018 (ኢዜአ)፦የPulse of Africa ሚዲያ በአፍሪካ ቀዳሚ እና ተፈላጊ የመሆን ህልሙ እንዲሳካ በትጋት መስራት እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) Pulse of Africa ሚዲያ ስራን ዛሬ በይፋ አስጀምረዋል።


 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አፍሪካ ትልቅ ሳለች ትንሽ መስላ እንድትታይ ያደረጋት ዋንኛ ምክንያት የአፍሪካ ሀገራት በትርክት ጭንቅላትን የመመገብ ዝግጁነት ውስን በመሆኑ ነው ብለዋል።

ባለፉት ሰባት ዓመታት በተለያዩ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን አፍሪካን የሚመጥኑ ትላልቅ መሰረተ ልማቶች መገንባታቸውን አውስተዋል።

ዛሬ በይፋ ስራ ያስጀመሩት የ Pulse of Africa ሚዲያ በቀላሉ ሊታይ እንደማይገባም አስገንዝበዋል።

የ Pulse of Africa ሚዲያ በጥቂት ዓመታት ውስጥ በአፍሪካ ቀደምት እና ታዋቂ ከሆኑ ሚዲያዎች አንዱ ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

የአንድ ሀገር ሚዲያ እድገት ከሀገራት ኢኮኖሚ እድገት ጋር የተሳሰረ መሆኑን ገልጸው ኢትዮጵያ በማንሰራራት ላይ እንደምትገኝም አመልክተዋል።

የዛሬ 10 ዓመት የምትኖረው ኢትዮጵያ በአፍሪካ በብዙ ነገር ግንባር ቀደም ትሆናለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያኔ ትርክት መገንባት የመሻት ጉዳይ ሳይሆን የኃላፊነት ጉዳይ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋ እያደገ ሲሄድ በአፍሪካ ትርክት ውስጥ ጉልህ ስፍራ መጫወት ኃላፊነቷ መሆኑ አይቀሬ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በአፍሪካ ታሪክ ከፍተኛ አደጋ የነበረው ከውጭ እየመጡ ያሉ በዝባዥ ኃይሎች አፍሪካን እንዳይበዘብዙ መከላከል ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በግንባር ቀደምትነት በመሰለፍ ከአድዋ ታላቁን ብስራት ያሰማችው በልጆቿ ደምና አጥንት በከፍተኛ ተጋድሎ ለበርካታ የአፍሪካ ሀገራት ነጻ መውጣት ትልቅ ሚና መጫወቷን አውስተዋል።

አፍሪካ ከተጋድሎው በኋላ ከመከላከል ወደ ልማት እና ብልጽግና መሸጋገር እንደነበረባት ጠቅሰው ለአፍሪካ ድምጽ የመሆንን ጉዳይ አፍሪካውያን ከኢትዮጵያ ሁሌ የሚጠብቁት ነገር እንደሆነም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ ከራሷ ተሻግራ የአፍሪካ ድምጽ ለመሆን እየሰራች መሆኗንም ነው የገለጹት።

አፍሪካ ምድረ ቀደምት፣ ከፍተኛ የከርሰ ምድር ሀብት ያላትና ለመፍጠር የሚያበቃ ጭንቅላት ያላቸው ወጣቶች አህጉር መሆኗን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ከራሷ በመሻገር የአፍሪካን ትልቅነት፣ሀብታምነት፣የማድረግ አቅም እንዲሁም አፍሪካውያን ሲደመሩ የተሻለ ነገር ማምጣት እንደሚችሉ የ Pulse of Africa ሚዲያ በብዙ ነገር እንደሚያስተምር ተናግረዋል።

Pulse of Africa ከበቂ በላይ መሰረተ ልማት መገንባቱን ገልጸው፥ ሚዲያው ምርምር ላይ የተመሰረተ ዘገባዎችን ካከናወነ በአፍሪካ ቀዳሚ ይሆናል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

የPulse of Africa ሚዲያ በአፍሪካ ቀዳሚ እና ተፈላጊ የመሆን ህልሙ ፍሬያማ እንዲሆንና እንዲሳካ በትጋት መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

Pulse of Africa የአፍሪካ ድምጽ ነው፤የአፍሪካ ምስል፣ ባህል እና ሀብት መገለጫ ነው ብለዋል።

ከአፍሪካ ወንድሞቻችን ጋር በሁሉም ነገር በትብብር እና በመደመር በጋራ መቆም ይገባናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ረገድም Pulse of Africa የበኩሉን ሚና እንዲወጣ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም