ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመዲናዋ አዳዲስ የተገነቡ የቱሪዝም መዳረሻዎችን የበለጠ ለማስተዋወቅ ትልቅ ሚና አለው -ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 27/2018 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመዲናዋ በኮሪደርና የወንዝ ዳርቻዎች ልማት የለሙ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻ ስራዎችን የበለጠ ለማስተዋወቅ ትልቅ ሚና እንዳለው የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመዋል።

ስምምነቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው ፈርመውታል።

የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመዲናዋ እየተከናወኑ ላሉ የልማት ስራዎች ትልቅ እገዛ ሲያደርግ ቆይቷል።

ከተማ አስተዳደሩ መዲናዋን ምቹ በማድረግ አለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሁም የቱሪስት መዳረሻነቷን ይበልጥ ለማሳደግ በሚሰራቸው ስራዎች የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስተዋፅኦ የጎላ መሆኑን ገልፀዋል።


 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመዲናዋ የሚከናወኑ ሰው ተኮር ስራዎችን እየደገፈ መሆኑን ገልፀው፤ በሁለት የምገባ ማዕከላት በቋሚነት ምግብ በማቅረብ በርካቶችን እየመገበ መሆኑን ጠቁመዋል።

ለአቅመ ደካሞችና የሀገር ባውለታዎች የተገነቡ ቤቶች ስራ ላይም አሻራውን ማኖሩን አክለዋል።

ስምምነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድን በመዲናዋ እየተከናወኑ በሚገኙ የልማት ስራዎች ላይ አጋር ማድረግ፣ በኮሪደርና የወንዝ ዳርቻዎች ልማት የለሙ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ማስተዋወቅ፣ በዚህም የስቶፕ ኦቨር ቱሪዝም ተጠቃሚነትን ማሳደግ፣ የከተማዋን አዲስ መለያ የሆነውን new face of Africaን ማስተዋወቅ የሚያስችል ነው ብለዋል።

ከተማ አስተዳደሩም አየር መንገዱ ሀገርን ለማሳደግ በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው፤ ከተማ አስተዳደሩ እያከናወናቸው ያሉ ስራዎች የሚያስደንቁ መሆናቸውን ገልፀዋል።

በመዲናዋ እየተከናወኑ ያሉ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች ልማት የቱሪስቶችን የቆይታ ጊዜ ማራዘም የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል።

በዚህም አየር መንገዱ ካሁን ቀደም ሲያደርጋቸው የነበሩትን ድጋፎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም