የአምባሳደር አየለ ሊሬ ሥርዓተ ቀብር ተፈጸመ - ኢዜአ አማርኛ
የአምባሳደር አየለ ሊሬ ሥርዓተ ቀብር ተፈጸመ
አዲስ አበባ፤መስከረም 27/2018 (ኢዜአ)፡-በኩባ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር የነበሩት አየለ ሊሬ ሥርዓተ ቀብር በአዲስ አበባ ቅዱስ ዮሴፍ ቤተክርስቲያን የፕሮቴስታንት መካነ መቃብር ተፈጽሟል፡፡
በቀብር ሥርዓቱ ላይ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ፣ የቀድሞዋ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ሀላፊዎች፣ አምባሳደሮችና ወዳጅ ዘመዶቻቸው ተገኝተዋል።
አምባሳደር አየለ ሊሬ ከአባታቸው ሊሬ ጂጃሞ እና ከእናታቸው ወይዘሮ አንድቤ ከፋቶ በ1958 ዓ.ም በሀዲያ ዞን እንደተወለዱ የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል፡፡
አምባሳደር አየለ ሊሬ ለረጅም ዓመታት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በተለያዩ ደረጃዎች ያገለገሉ ሲሆን እስከ ህልፈታቸው ድረስ በኩባ የኢትዮጵያ አምባሰደር ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡
ከ1986 ጀምሮ ከባለሙያነት እስከ አመራርነትና አምባሳደርነት በተለያዩ የሥራ ክፍሎች ሲያገለግሉ እንደነበርም የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል፡፡
አምባሳደሩ በኩባ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሆነው ከማገልገላቸውም በተጨማሪ የጃማይካ፣ዶሚኒካን ሪፐብሊክ፣ ሁንዱራንስ እና ሜክሲኮን ጨምሮ በካሪቢያ ሀገሮች የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስከበር ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡
አምባሳደር አየለ ሊሬ የአንድ ወንድና የሁለት ሴት ልጆች አባትም ነበሩ፡፡
የአምባሳደር አየለ ሊሬ የቀብር ሥነ-ሥርዓት ዛሬ መስከረም 27 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ቅዱስ ዮሴፍ ቤተ ክርስቲያን የፕሮቴስታንት መካነ መቃብር ተፈጽሟል፡