ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በአማራ ክልል የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም እያሳደገው ነው- ቢሮው

ባህር ዳር፤ መስከረም 27/2018(ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የክልሉን አምራች ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም እያሳደገው መምጣቱን የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው ባዘጋጀው የ10 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ላይ ከፋይናንስ፣ ከመሰረተ ልማት እና ከሰው ሃይል አቅራቢ ተቋማት ጋር ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ተወያይቷል።


 

የቢሮው ኃላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ባለሃብቶችንና መንግስትን በማቀራረብ በዘርፉ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን ለመፍታት እያስቻለ ነው።

በዚህም ንቅናቄው ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ከ44 ነጥብ 6 በመቶ ወደ 59 ነጥብ 2 በመቶ እንዳሳደገው ገልጸዋል።

የዛሬው ውይይት ዓላማም በመሰረተ ልማት፣ በፋይናንስና ለዘርፉ የሚመጥን የሰው ሀይል በማቅረብ ረገድ የሚስተዋሉ  ክፍተቶችን በመሙላት የክልሉን እድገት ለማፋጠንና ህዝብን ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የአማራ ሪጅን ማስተባበሪያ ቢሮ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰለሞን ጣሰው እንደገለጹት የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት እድገቱን ለማፋጠን የሚያስችል የኤሌክትሪክ ሃይል ለማቅረብ ሲሰራ ቆይቷል።

በዘርፉ ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ አገልግሎቱ የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ገልጸው፣ በቀጣይም የኢንዱስትሪ ዘርፉ የሚያስፈልገውን የሃይል ፍላጎት መሰረት ያደረገ ሥራ እንደሚከናወን አረጋግጠዋል።

የአማራ ባንክ ባህር ዳር ዲስትሪክት ሥራ አስኪያጅ አቶ ጥበቡ አሰፋ ባንኩ ከተመሰረተ አጭር ጊዜ ቢሆነውም የ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ብድር በማቅረብ ለዘርፉ እድገት የድርሻውን መወጣቱን ተናግረዋል።

የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መስፋፋት በተለይ ለወጣቶች አዳዲስ የሥራ ዕድል መፍጠር ስለሚያስችል ባንኩ የፋይናንስ አቅርቦቱን ከዚህም በላይ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በአማራ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት 486 ቢሊዮን ብር ካፒታል የሚያስመዘግቡ ባለሀብቶችን ለመሳብ ግብ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም