ዩኒቨርሲቲው በግብርናው መስክ የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ የተለያዩ የጥናትና ምርምር ስራዎችን እያከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲው በግብርናው መስክ የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ የተለያዩ የጥናትና ምርምር ስራዎችን እያከናወነ ነው
መቱ፤ መስከረም 27/2018 (ኢዜአ) ፡-መቱ ዩኒቨርሲቲ በግብርናው መስክ የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ የተለያዩ የጥናትና ምርምር ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዓለሙ ዲሳሳ (ዶ/ር) ተናገሩ።
መቱ ዩኒቨርሲቲ የጥናትና ምርምር የባለድርሻ አካላት መድረክ እየተካሄደ ሲሆን በመድረኩ በተለያዩ በዩኒቨርሲቲው ምሁራን የተሰሩና ወደ ትግበራ ለመግባት በዝግጅት ላይ የሚገኙ የምርምር ውጤቶች ዋና ዋና ሐሳቦች ቀርበው ውይይት እየተደረገባቸው ይገኛሉ።
የመቱ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዓለሙ ዲሳሳ (ዶ/ር) ዩኒቨርሲቲው በተለይ በግብርናው መስክ የተለያዩ የጥናትና ምርምር ስራዎች መከናወኑን አስረድተዋል።
የምርምር ስራዎቹ እንደሀገር የተቀረጹ የግብርና ኢኒሼቲቮችን የሚያግዙ፣ ለውጤታማነቱም አቅም የሚጨምሩ መሆናቸውም አንስተዋል።
በዚሁ መሰረት ምርጥ የሰብል ዝርያዎችን በማባዛት፣ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ቨርሚ ኮምፖስት በማምረት፣ በምርጥ የወተት ላሞች፣ በዶሮ እርባታ፣ በንብ ማነብ፣ በኃይል አቅርቦትና በሌሎች ላይ የተዘጋጁ ዘጠኝ የምርምር ውጤቶች እንዳሉም ተገልፅዋል።
በማሕበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ፤ በትምህርት እንዲሁም የአገልግሎት አሰጣጥን በሚያቀላጥፉ የምርምር ስራዎች ላይ ተግባራዊ እየተደረጉ እንደሚገኙም አንስተዋል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሀገራዊ ምርምርና ልማት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሀብታሙ አበራ (ዶ/ር) ዩኒቨርሲቲው እየሰራ ያለው ነገን ታሳቢ ያደረጉ እና ምርታማነትን ለመጨመር የሚያስችሉ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ነው።
የምርምር ስራዎቹ የግብርና ምርታማነትን ለመጨመርና የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል ተስፋ የሚጣልባቸው እንደሆኑም አንስተዋል።
በዚህም ሚኒስቴሩ ድጋፍና ክትትሉን እንደሚያጠናክርም ገልጸዋል።