ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ቡና በዓለም አቀፍ ገበያ ተፈላጊና ተመራጭ ነው-የውጭ ዜጎችና ዳያስፖራዎች

ዲላ፤መስከረም 27/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ቡና ተፈጥሯዊ ጣዕሙ የተለየ በመሆኑ በዓለም አቀፍ ገበያ ተፈላጊነቱና ተመራጭነቱ ከፍተኛ መሆኑን የውጭ ዜጎችና ዳያስፖራዎች ገለጹ።

የቡናን ተፈጥሯዊ ጣዕም በመጠበቅና እሴት ጨምሮ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ተፈላጊነትንና ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ እየተሰራ እንደሚገኝም ተመላክቷል።

የውጭና የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች በተገኙበት የጌዴኦ ዞን የኢኮኖሚ እድገት ፎረም መካሄዱ የሚታወስ ነው።

በፎረሙ ላይ የተሳተፉ የውጭ ዜጎችና ዳያስፖራዎች የኢትዮጵያ ቡና ተፈጥሯዊ ጣዕሙ የተለየ በመሆኑ በዓለም አቀፍ ገበያ ተፈላጊነትና ተመራጭነቱ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

ከፎረሙ ተሳታፊዎች መካከል ከአሜሪካ የመጡት ዊልያም ኢሲሚዝ ለኢዜአ እንደገለጹት የኢትዮጵያ ቡና ተፈጥሯዊ ጣዕሙ የተለየ ነው።

በዓለም አቀፍ ገበያ ጭምር ተፈላጊና ተመራጭነቱ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፥በሚኖሩበት አሜሪካ የኢትዮጵያና የኮሎንቢያ ቡናን በስፋት እንደሚጠቀሙ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያን ቡና ከመጠጣት ባለፈ እዚህ መጥተው የቡና ልማቱን በአካል በመመልከታቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል።

በጌዴኦ ዞን የይርጋጨፌ ልዩ ጣዕም ቡና የኢትዮጵያ ቡና የተለየ ለመሆኑ ጥሩ ማሳያ ነው ያሉት ዊልያም ኢሲሚዝ፣ የኢትዮጵያን የቡና አቅም ለዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ በአግባቡ ማስተዋወቅ ከተቻለ የተሻለ ገበያ መፍጠር ይቻላል ብለዋል።

በቀጣይ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በግብርና ዘርፎች በተለይ በቡና ልማት ለመሰማራት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያን ልዩ ጣዕም ቡና እሴት ጨምሮ ለውጭ ገበያ ማቅረብ አዋጭ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በአሜሪካ መርክ የመድሃኒት ድርጅት መሪ ሳይንቲስትና የጌዴኦ ዲያስፖራ ማህበር ሰብሳቢ ሄኖክ ታደሰ (ዶ/ር) ናቸው።

ማህበሩ በጌዴኦ ዞን በቡና፣ በእንሰት ተረፈ ምርትና በቱሪዝም ዘርፎች ያሉ እምቅ የኢንቨስትመንት አቅሞችን ለመጠቀም በአግሮ ኢንዱስትሪ ዘርፎች እየተሳተፈ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

በቀጣይ የኢንቨስትመንት ተሳትፎውን በማጠናከር ተጠቃሚ ለመሆን እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

ሬማ የቡና ቀማሾች ማህበር ሰብሳቢ አቶ አቤነዘር ሙሉጌታ በበኩላቸው፥ ቡናን ተፈጥሯዊ ጣዕም ጠብቆና እሴት ጨምሮ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ተፈላጊነቱንና ተወዳዳሪነቱን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የተቆላ፣የተፈጨና በፈሳሽ መልክ የተዘጋጁ ከ600 ኪሎ ግራም በላይ እሴት የተጨመረበት ቡና ለተመረጡ የውጭ ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ይህም የኢትዮጵያን ቡና ተፈጥሯዊ ጣዕም ጠብቆ በማቅረብ ሀገርን ከማስተዋወቅ ባለፈ የውጭ ገዥዎች የመግዛት ፍላጎታቸው እንዲጨምርና ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ማድረጉን አስረድተዋል።

በዞኑ እሴት በሚጨምሩ የኢንቨስትመን ዘርፎች የግሉን ባለሃብት ተሳትፎ ለማሳደግ ትኩረት መሰጠቱን ያነሱት ደግሞ የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር) ናቸው።

በተለይ ዞኑ በቡና፣ በእንሰት ልማትና ተረፈ ምርት እንዲሁም በቱሪዝምና ማዕድን ያሉትን ጸጋዎች ከኢንዱስትሪው ጋር ለማስተሳሰር የግሉን ባለሀብትና የዳያስፖራውን እውቀት፣ ልምድና ካፒታል ለመጠቀም እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

በዚህም ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ በተደረገ ጥረት ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 150 አልሚዎች ወደ ሥራ ገብተዋል ብለዋል።

በተያዘው ዓመት ይህንን ለማጠናከር የመሬት አቅርቦት ሥራ በማጠናቀቅ አልሚዎችን እየጠበቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደርና ሥራና ክህሎት ቢሮ ሃላፊ አበባየሁ ታደሰ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ በክልሉ ክህሎት መር ስራና የቁጠባ ባህል እንዲዳብር የተደረገው ጥረት የኢንቨስትመንት አቅምን እያሳደገ ነው።

በቀጣይ ቀልጣፋ አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ በአግሮ ኢንዱስትሪ ዘርፎች የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቱን ተሳትፎ ለማጠናከር መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም