ቀጥታ፡

በክልሉ የትምህርት ዘርፉን ውጤታማነት ለማሳደግ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ መጠናከር አለበት

ነቀምቴ፤ መስከረም 27/2018(ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል የትምህርት ዘርፉን ጥራትና ውጤታማነት ለማሳደግ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ማደግ አለበት ሲሉ የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አወሉ አብዲ ተናገሩ።

ምክትል ፕሬዚዳንቱን አቶ አወሉ አብዲን ጨምሮ የብሔራዊ ባንክ ገዢ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) እና ሌሎች የክልል የሥራ ሃላፊዎች የተለያዩ እንግዶች በተገኙበት የቢፍቱ ነቀምቴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ የተገነቡ ተጨማሪ የመማሪያ ህንፃዎች ተመርቀዋል።


 

በምረቃው ላይ የተገኙት የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አወሉ አብዲ፣ የትምህርት ዘርፉን ጥራትና ውጤታማነት ለማሳደግ የክልሉ መንግስት ከሚያከናውናቸው ተግባራት ባሻገር የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ማደግ አለበት ብለዋል።


 

የተሻለ የትምህርት ስርዓት ከተዘረጋ የሀገር ልማትን የሚያፋጥን ትውልድ መገንባት እንደሚቻል አንስተው ለዚህ ደግሞ የትምህርት ዘርፉን ውጤታማነት ማሳደግ ይገባል ነው ያሉት።

በተለይም ሀገራችን ያላትን ምቹ የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም እና የሀገርን ኢኮኖሚ ለማሳደግ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ መረባረብ እንደሚገባም አመልክተዋል።


 

ተጨማሪ መማሪያ ህንጻዎቹ የተገነቡት በፀሐይ ፋውንዴሽን አማካኝነት መሆኑን ጠቅሰው ለፈውንዴሽኑ ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በበኩላቸው  በቢፍቱ ነቀምቴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተጨማሪ ባለ ሁለት  ወለል ህንጻ የመማሪያ ክፍሎች በ45 ሚሊዮን ብር ተገንብቶ ለአካባቢው ነዋሪዎች መሰጠቱን አውስተዋል።


 

የተማረ የሰው ሃይል ያላት ሀገር በእድገትና ስልጣኔ ጎዳና ላይ በቀላሉ ስኬታማ መሆን ስለምትችል ሁሉም ትኩረት ሰጥቶ ሊረባረብ እንደሚገባም ተናግረዋል።

በተማሩበት ትምህርት ቤት ደረጃውን የጠበቀ የመማሪያ ክፍሎች መገንባታቸውን አንስተው ሌሎች ባለድርሻ አካላት በመሰል ስራዎች እንዲሳተፉ ጠይቀዋል።

የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ሃላፊ  ቶላ በሪሶ (ዶ/ር) በበኩላቸው በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የሚያግዙ የተለያዩ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን ተናግረዋል።

ከነዚህ ጥረቶች መካከል የትምህርት መሰረተ ልማትን የማሟላት እና የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ግንባታ በስፋት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።

መንግስት የጀመራቸውን እርምጃዎች በተሻለ መልኩ ለማስቀጠል ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም