ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት መሰረት መስከረም 29 ቀን 2018 ዓም የንግድ ትግበራዋን ልትጀምር ነው

አዲስ አበባ፤መስከረም 27/2018 (ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያ በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት መሰረት መስከረም 29 ቀን 2018 ዓም የተለያዩ ምርቶችን በመላክ የንግድ ትግበራዋን እንደምትጀምር የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ።

በማስጀመሪያ መርሀ ግብሩ ላይ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች እና የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና የስራ ሀላፊዎች እንደሚታደሙ ተገልጿል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ያስሚን ወሀብረቢ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ግብይትን ለማስጀመር በርካታ ተግባራት ሲከናወኑ ቆይተዋል።

ኢትዮጵያ ስምምነቱን በመፈረም ቁርጠኝነቷን ያሳየች መሆኑን ገልጸው፤በአሁኑ ወቅት የግብይት ስርዓቱን ለማስጀመር ዝግጅት የተጠናቀቀ መሆኑን ገልፀዋል።

ነፃ የንግድ ግብይት መጀመሩ በኢትዮጵያ በወጪ ንግድ ዘርፍ እየታየ ያለውን እድገት ለማስቀጠል ፋይዳው የጎላ መሆኑን ገልጸው፤የሀገር ውስጥ የንግድ እንቅስቃሴን ለማሳደግ የሚያግዝ እንደሆነ አብራርተዋል።

ግብይቱ መጀመሩ ኢትዮጵያ ቀጣናውን በኢኮኖሚ ለማስተሳሰር የምታደርገውን ጥረት የሚያፋጥን መሆኑን ገልፀዋል።

በዚህም ግብይቱ በአፍሪካ ከተለያዩ ሀገራት ጋር የሚደረግ ሲሆን መስከረም 29 ቀን 2018 ዓም በሚካሔደው የጭነት የማስጀመሪያ መርሃ ግብር ምርቶችን የመላክ ስራው እንደሚጀመር ተናግረዋል።

በዚህም በኢትዮጵያ አየር መንገድ ካርጎ ሥጋ፣ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በየብስ ትራንፖርት ቡና፣ የጥራጥሬ ምርቶችና የቅባት እህሎች ወደ ኬንያ፣ ሶማሊያ እና ደቡብ አፍሪካ እንደሚላክ አብራርተዋል፡፡

ስምምነቱ ለነጋዴዎች፣ለወጣቶች፣ለስራ ፈጣሪዎችና ሴቶች ተጨማሪ የስራ እድል ይዞ ከመምጣቱ ባሻገር ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እንደሚረዳም ነው የጠቀሱት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም