በደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት እየተከናወኑ የሚገኙ የተቀናጁ ስራዎች ጤናማ ትውልድ ለመፍጠር እያገዙ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት እየተከናወኑ የሚገኙ የተቀናጁ ስራዎች ጤናማ ትውልድ ለመፍጠር እያገዙ ናቸው
ድሬደዋ፣ መስከረም 27/2018(ኢዜአ) በደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ዘርፍ እየተከናወኑ የሚገኙ የተቀናጁ ስራዎች ጤናማ ማህበረሰብ እና ትውልድ ለመፍጠር እያገዙ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሳህረላ አብዱላሂ ተናገሩ።
በዘንድሮ ዓመት ከደምና ቲሹ ባሻገር ብሔራዊ የአካል ንቅለ ተከላ አገልግሎት ለመስጠት ትኩረት መደረጉም ተመላክቷል።
"ዲጂታላይዜሽንና ፈጠራ ለጠንካራ የደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት" በሚል መሪ ሃሳብ የክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የዘርፉ አመራርና ባለሙያዎች የተሳተፉበት 13ኛ ዓመታዊ የደምና ህብረ ህዋስ ባንኮች ጉባዔ በድሬደዋ ዛሬ መካሄድ ጀምሯል።
በጉባዔው ላይ የተሳተፉት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሳህረላ አብዱላሂ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ ጤናማ ማህበረሰብ ለመፍጠርና የሰዎችን ህይወት ለመታደግ በዘርፉ እየተከናወኑ የሚገኙ የተናበቡና የተቀናጁ ስራዎች አበረታች ናቸው።
ደም በመሰብሰብ፣ በደምና አካላት አቅርቦት እንዲሁም በዓይን ኮርኒያ ህብረ ህዋስ አሰባሰብ የተሰሩ የተቀናጁ ተግባራትን አድንቀው አመራሮችና ባለሙያዎች እነዚህን ፍሬያማ ተግባራት የበለጠ እንዲያሳድጉ እየተካሄደ የሚገኘው ጉባዔ ጥሩ መደላድልን እንደሚፈጥር አንስተዋል።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታዋ ገለፃ ሚኒስቴሩ የደምና የህብረ ህዋስ አገልግሎትን በማስፋፋትና በዲጂታል የፈጠራ አሠራሮች በመደገፍ የላቀ ውጤት እንዲመዘገብ በቁርጠኝነት ይሰራል።
በዘርፉ የሚፈለገውን ሀገራዊ ለውጥ ለማስመዝገብ ቀጣይነት ያለው ሙያዊ ስልጠና በመስጠት እንዲሁም የዕውቅናና የጥራት ማረጋገጫ ስርዓት በመዘርጋት በትኩረት እንደሚሰራም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አሸናፊ ታዘበው በበኩላቸው በተጠናቀቀው ዓመት ከከተሞችና ከክልሎች ማዕከላት ጋር በመቀናጀት ተደራሽና ጥራት ያላቸው አገልግሎቶች ለህብረተሰቡ ተሰጥቷል።
በመናበብ በተከናወኑ ተግባራትም ጤናማ ትውልድ የመፍጠሩን ጉዞ ለማሳካት የሚያስችሉ ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።
አገልግሎቶችን ዲጂታላይዝ የሚያደርግና ሁሉንም የክልሎች የደም ባንኮችን የሚያገናኝ ስርዓት እየተገነባ መሆኑን ጠቅሰው ይሄ ዘመናዊ አሠራር ከደም ለጋሾች እስከ ተቀባዮች ያለውን ሂደት በቅፅበት በመከታተል የተሻለ ውጤት ለማምጣት እንደሚያስችል ተናግረዋል።
በዘንድሮ በጀት አመት ከደምና ከ'ቲሹ ባሻገር ብሔራዊ የአካል ንቅለ ተከላ አገልግሎቶችን በመስጠት በጤናው ዘርፍ መሠረታዊ ለውጥ ለማስመዝገብ በትኩረት እንደሚሰራም ተናግረዋል።
አስተዳደሩ የደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት በማቋቋምና ደምን ከበጎ ፈቃደኞች በመሰብሰብ ጤናማ ማህበረሰብ ለመፍጠር በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ የገለፁት ደግሞ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ናቸዉ።
ከኢትዮጵያ ደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ጋር በመቀናጀት እየተከናወነ የሚገኘውን የተናበበ ስራን በማጠናከር በዘርፉ የተሻለ ለውጥ እንዲመዘገብ በቁርጠኝነት ይሰራል ብለዋል።
እየተካሄደ በሚገኘው ዓመታዊ ጉባኤ ላይ በ2017 በጀት ዓመት በዘርፉ የተሻለ አፈፃፀም ላስመዘገቡ ክልሎችና የደም ባንክ ተቋማት ዕውቅናና ሽልማት ተበርክቷል ።
በዛሬው ዕለት ሚኒስትር ዴኤታዋና ሌሎች አመራሮች በድሬደዋ ለደምና ህዋስ አገልግሎት መስጫ የሚያገለግል ዘመናዊና ሁለገብ ህንፃ ግንባታ ማስጀመራቸው መዘገባችን ይታወሳል።