የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በኮሪደርና የወንዝ ዳርቻዎች ልማት የለሙ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን የማስተዋወቅ ስራ በጋራ ሊሰሩ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በኮሪደርና የወንዝ ዳርቻዎች ልማት የለሙ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን የማስተዋወቅ ስራ በጋራ ሊሰሩ ነው
አዲስ አበባ፤ መስከረም 27/2018 (ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በከተማዋ የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻዎች ልማት የለሙ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን የማስተዋወቅ ስራ በጋራ እንደሚሰሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባስተላለፉት መልዕክት የሀገራችን ኩራት ከሆነው የኢትዮዽያ አየር መንገድ ግሩፕ ጋር በጋራ በምንሰራባቸው ጉዳዮች ላይ ዛሬ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመናል ብለዋል።
ኢትዮጵያውያንን ከዓለም ጋር ከሚያገናኛው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው እና ማኔጅመንታቸው የወንዝ ዳርቻ እና የኮሪደር ልማትን ከጎበኙ በኋላ በተደራጀ እና በተቀናጀ መልክ በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸውን ጠቅሰዋል።
ስምምነቱ በዋናነት በከተማችን የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻዎች ልማት የለሙ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን የማስተዋወቅ ስራ በጋራ ለመስራት የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል።
በዚህም የስቶፕ ኦቨር ቱሪዝም Stop Over Tourism ተጠቃሚነትን ማሳደግ፣ የከተማዋ አዲስ መለያ የሆነውን New Face of Africaን ከማስተዋወቅና የአቪየሽን ደህንነትን ከማረጋገጥ በተጨማሪም በከተማው የተለያዩ ማህበራዊና ሰው ተኮር ስራዎችን በጋራ መስራት ላይ ያተኮረ ነው ብለዋል።
አየር መንገዱ በከተማዋ በሚሰሩ ሰው ተኮር የልማት ስራዎች እና በኮሪደር ልማት ላይ ለነበረው ድጋፍም አመስግነዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ለስምምነቶቹ ተፈፃሚነት ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ጋር ከከዚህ ቀደሙ በበለጠ ተቀራርቦ የሚሰራ ይሆናል ሲሉም ገልጸዋል፡፡