በኢትዮጵያ የተገነባው ዘመናዊና ጠንካራ ሰራዊት የሀገርን ክብርና ሉአላዊነት በአስተማማኝ መልኩ የሚጠብቅ ነው-ጄኔራል አበባው ታደሰ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የተገነባው ዘመናዊና ጠንካራ ሰራዊት የሀገርን ክብርና ሉአላዊነት በአስተማማኝ መልኩ የሚጠብቅ ነው-ጄኔራል አበባው ታደሰ

ባቱ ፤መስከረም 27/2018(ኢዜአ)፡-በኢትዮጵያ የተገነባው ዘመናዊና ጠንካራ የመከላከያ ሰራዊት የሀገርን ክብርና ሉአላዊነት በአስተማማኝ መልኩ የሚጠብቅ መሆኑን የጦር ሃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ ገለጹ።
የሀገር መከላከያ ሰራዊት የደቡብ ዕዝ 21ኛ ጉና ክፍለ ጦር 30ኛ የምስረታ በዓል በኦሮሚያ ክልል ባቱ ከተማ ከፍተኛ ወታዳራዊ መኮንኖች፣የመንግስት የስራ ሃላፊዎች እና ሌሎችም ታዳሚዎች በተገኙበት ተከብሯል።
በዚሁ ሁነት ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የጦር ሃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ፤የሀገር መከላከያ ሰራዊት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ፣በብቃትና ጀግንነቱ ጭምር የኢትዮጵያ አስተማማኝ አለኝታ መሆኑን ገልጸዋል።
የውስጥ ባንዳዎችንና የውጭ ጠላቶችን ከንቱ ህልሞች በማምከን ኢትዮጵያ ተከብራና ሉአላዊነቷ ተከብሮ እንድትዘልቅ ያደረገ መሆኑንም አንስተዋል።
በኢትዮጵያ የተገነባው ዘመናዊና ጠንካራ ሰራዊት የሀገርን ክብርና ሉአላዊነት በአስተማማኝ መልኩ የሚጠብቅ ነው ሲሉም አረጋግጠዋል።
የደቡብ ዕዝ 21ኛ ጉና ክፍለ ጦር ባለፉት 30 ዓመታት ሰላምና ደህንነትን ከማረጋገጥ ባለፈ በርካታ ወታደራዊ መሪ ያፈራና ትምህርታዊ ልምድ የተወሰደበት የሰራዊት ክፍል መሆኑንም አንስተዋል።
የደቡብ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ሰለሞን ኢተፋ፥ ክፍለ ጦሩ የፀረ ሰላም ሃይሎችን የሽብር እንቅስቃሴ በማክሸፍ አኩሪ ገድል በመፈፀም ሀገርን በማፅናት በኩል የላቀ ሚናውን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።
ክፍለ ጦሩ የተለያዩ ክፍለ ጦሮች እንዲመሰረቱ ልምድና መሰረት በመሆን እያገለገለ መሆኑንም ተናግረዋል።
የባቱ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አህመዲን እስማኤል ፤ የከተማዋና አከባቢዋ ሕብረተሰብ የኢትዮጵያ ጥንካሬ መገለጫ ከሆነው የሀገር መከላከያ ጎን ነው ብለዋል።
የአካባቢው ሕብረተሰብ ሰላምን በማፅናት ልማትና ዕድገት በተሻለ ደረጃ እያስቀጠለ ነው ያሉት ከንቲባው፥ባቱና የአካባቢዋ ማህበረሰብ ሰላሙን በመጠበቅ ረገድ ከሀገር መከላከያና ከፀጥታ አካላት ጋር በትብብር በመስራት ሰላምን በማረጋገጥ የበኩላቸውን እንደተወጡ ገልጸዋል።
በክበረ በዓሉ ላይ የሀገር ህልውና በማስጠበቅ ላይ ለተሰውና በክብር ለተሰናበቱ የክፍለ ጦሩ አባላት ቤተሰቦች እውቅና ተሰጥቷል።