ቀጥታ፡

በክረምት ወራት የህዝብ ውክልና ስራ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ውይይቶች ተካሂደዋል - የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት

አዲስ አበባ፤ መስከረም 27/2018 (ኢዜአ)፡- በክረምት ወራት የህዝብ ውክልና ስራ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጡ ስራዎች ዙሪያ ውጤታማ ውይይቶች መካሄዳቸውን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለጹ።

ስድስተኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አምስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን መክፈቻ ሥነ- ሥርዓት ትናንት ተካሂዷል።


 

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በክረምት ወራት ከሚያከናውናቸው ስራዎች አንዱ የህዝብ ውክልና ስራዎች መሆኑ ይታወቃል።

የምክር ቤቱ አባላት በሚያከናውኑት የህዝብ ውክልና ሥራ እስከታች ባሉ መዋቅሮች ከህብረተሰቡ ጋር  ውይይት ያደርጋሉ።

በዚህም ከመራጮቻቸው ጋር በሚነሱ የመሠረተ ልማት እንዲሁም ሌሎች የመልካም አስተዳደር እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ይወያያሉ።

ኢዜአ የምክርቤቱ አባላት የክረምት የህዝብ ውክልና ስራ ምን ይመስላል ሲል አባላቱን አነጋግሯል።

የምክር ቤት አባል ረዳት ፕሮፌሰር ገነነ ገረቡ በክረምት ወራት የህዝብ ውክልና ስራ በተገቢው መንገድ መከናወኑን ገልጸዋል።

እስከታችኛው መዋቅር ድረስ በመውረድ ህገ-መንግስቱን መነሻ ያደረጉ ስራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን ጠቁመዋል።

በበጀት አመቱም ከህብረተሰቡ የተነሱ ጥያቄዎች በአግባቡ ለመንግስት ደርሰው ምላሽ እንዲያገኙ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጭ ፋጡማ አሊ በበኩላቸው በህዝብ ውክልና ስራዎች በርካታ ስራዎች እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

እስከታችኛው የመንግስት መዋቅር ድረስ በመውረድ ውጤታማ ውይይቶች ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

የተለያዩ ፈተናዎች ቢኖሩም በፈተና ውስጥ ድል መኖሩን ተመልክተናል ያሉት አባሏ በቀጣይም በመንግስት የተቀመጡ አቅጣጫዎች ተፈጻሚ መሆናቸውን የምንከታተል እና የምንቆጣጠር ይሆናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም