ቀጥታ፡

የመንግስት የልማት አቅጣጫዎች የኢትዮጵያን ብልጽግና የሚያረጋግጡ ናቸው - የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት

አዲስ አበባ፤ መስከረም 27/2018 (ኢዜአ)፡- የ2018 በጀት ዓመት የመንግስት የልማት አቅጣጫዎች የልማት ጥያቄዎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ በመፍታት የኢትዮጵያን ብልጽግና የሚያረጋግጡ መሆናቸውን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለጹ።

ስድስተኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አምስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን መክፈቻ ሥነ- ሥርዓት ትናንት ተካሂዷል።

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ በዚሁ ወቅት ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር እንደገለጹት፤የኢትዮጵያን ዕድገትና ብልጽግናን ለማረጋገጥ በርካታ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው።


 

መንግስት መጪው ጊዜ አስተማማኝ እና በታሪክ የሚዘከር እንዲሆን የሚያስችሉ በርካታ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ አንስተዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁ፣ የአረንጓዴ አሻራ ትልም መስፋፋቱ እንዲሁም ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች መተግበራቸው በጉልህ የሚጠቀሱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የተፈጥሮ ጋዝ ሃብት ማውጣትና የመጠቀም ስራ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ትግበራ መግባቱ እና ሁለተኛው ምዕራፍ የተፈጥሮ ጋዝ ልማት መጀመሩ ሌላኛው ትልቅ ተግባር መሆኑን አስታውቀዋል።

ሀገርን ከማዳበሪያ ግዢ ጥገኝነት በማላቀቅ ለጎረቤት አገራት የሚተርፍ ግዙፍ የማዳበሪያ ማምረቻ ፋብሪካ ግንባታ መጀመሩ በጉልህ የሚጠቀስ ተግባር መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ የተጀመሩ የልማት እና ሌሎች ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የምክር ቤት አባል አጉ ደባን በመንግስት የተያዙ የልማት አቅጣጫዎች የኢትዮጵያን ብልጽግና የሚያረጋግጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

እንዲሁም በአጭር ጊዜ ውስጥ የህዝቡን የልማት ፍላጎት  የሚያሳኩ መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

በተጨማሪም በመንግስት የተቀመጡ የልማት ትልሞች የኢትዮጵያን የብልጽግና ተምሳሌትነት የሚያሳዩ እና በዓለም ላይ ያላትን ተደማጭነት የሚያጎለብቱ መሆናቸውን ጠቁመዋል። 

የምክር ቤቱ አባል አስና ሀንፍሬ በበኩላቸው፤ በዚህ በጀት ዓመት በመንግስት ይፋ የተደረጉ ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያን ከፍ የሚያደርጉ መሆናቸውን አንስተዋል።


 

በማዕድን እና በኤሌክትሪክ ሀይል ዘርፍ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ አቅም የሚያሳድጉ ናቸው ብለዋል።

እንዲሁም በማዳበሪያ እና ነዳጅ ላይ የተጀመሩ ስራዎች ከዚህ ቀደም በንግግር የቀሩና ለመስራትም የማይደፈሩ እንደነበሩ አስታውሰዋል።

እነዚህ እና መሰል የልማት ስራዎች የኢትዮጵያን ስም ከፍ የሚያደርጉና ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የምታደርገውን ጉዞ የሚያረጋግጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም