ቀጥታ፡

የኮንስትራክሽን ቁጥጥር መረጃ ሥርዓት የዘርፉን የመሰረተ ልማት ግንባታ በማሳለጥ ለሀገራዊ ኢኮኖሚ ዕድገት ሚናውን እንዲያሳድግ የሚያስችል ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 27/2018 (ኢዜአ)፡-የኮንስትራክሽን ቁጥጥር መረጃ ሥርዓት የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን የመሰረተ ልማት ግንባታን በማሳለጥ ለሀገራዊ ኢኮኖሚ ዕድገት ሚናውን እንዲያሳድግ የሚያስችል መሆኑን የከተማና እና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ገለጹ። 

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን እና የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር በጋራ ያለሙት አዲስ የግንባታ ቁጥጥር መረጃ ስርዓት ይፋ ተደረጓል።

የኮንስትራክሽን ቁጥጥር መረጃ ስርዓቱን የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ፣ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መስፍን ነገዎ (ዶ/ር) እና የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግሥት ሃሚድ ይፋ አድርገውታል። 

ይፋ የተደረገው የኮንስትራክሽን ቁጥጥር መረጃ ሥርዓት ግልፅነትና ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚያስችል መሆኑ ተጠቁሟል። 

የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር በቅርቡ ይፋ አድርጎ ወደ ተግባር የገባውን ሀገራዊ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ትራንስፎርሜሽን ኢኒሼቲቭ መሠረት ተደርጎ የለማ ሥርዓት መሆኑ ተጠቁሟል። 

ስርዓቱ በተበታተነ ሁኔታ እና በሰው ኃይል ይከናወን የነበረ የስራ ሂደትን ተናባቢ፣ የተዋሃደ፣ ወጥ እንዲሁም ዲጂታል ቴክኖሎጂ መር ወደ ሆነ አሰራር የማሳለጥ ዓላማ እንዳለውም ተገልጿል። 


 

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በዚሁ ወቅት፤ የኮንስትራክሽን ቁጥጥር መረጃ ሥርዓት በዘርፉ የሚሰጠው አገልግሎት በጥራት፣ ውጤታማ በሆነ መንገድ ብሎም ስራዎችን ለማዘመን የሚያስችል ነው ብለዋል። 

በመላ ሃገሪቱ የሚከናወኑ የግንባታ ቁጥጥር ሂደቶችን ዘላቂ፣ የተሟላ፣ ግልጽ ወጥ እና ወደ ተዋሃደ የዲጂታል አስተዳደር ስርዓት እንዲሸጋገር የሚያስችልም ነው ብለዋል። 

ግንባታዎችን በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቁ የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመው፤ ለሀገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ያላቸው አበርክቶም የላቀ እንዲሆን ያስችላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መስፍን ነገዎ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷  ስርዓቱ ደህንነቱ የተጠበቀ የመረጃ ሥርዓት እንዲኖር የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል።

የተቋሙን ቁልፍ ተግባራት በዲጂታል ስርዓት ማሳለጥ፣ ግልጽነትንና ተጠያቂነትን ማስፈን፣መረጃን ማዕከላዊ ማድረግ፣ ዳታ መር የሆነ አስተዳደርን የማስፈን እንዲሁም ጤናማና ደህንነቱ የተረጋገጠ ስርዓት እውን በማድረግ ረገድ የላቀ ሚና እንደሚጫወትም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም