የPulse of Africa ሚዲያ ሥራ መጀመር አፍሪካን በአሉታዊ ገጽታ የማቅረብ ሥራን ለመመከት ጠቃሚ ርምጃ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የPulse of Africa ሚዲያ ሥራ መጀመር አፍሪካን በአሉታዊ ገጽታ የማቅረብ ሥራን ለመመከት ጠቃሚ ርምጃ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ መስከረም 27/2018 (ኢዜአ)፡- የPulse of Africa ሚዲያ ሥራ መጀመር አፍሪካን በአሉታዊ ገጽታ የማቅረብ ሥራን ለመመከት ብሎም የራሳችንን ትርክት በራሳችን የመቅረጽ ተግባራችንን የምናፀናበት ጠቃሚ ርምጃ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ምንም እንኳ አፍሪካ ሰፊ እና እምቅ ሀብት ያላት አኅጉር ብትሆንም አብዛኛውን ጊዜ እንደ አነስተኛ እና አቅመቢስ ተደርጋ ትሳላለች ብለዋል።
በዚህ የተነሳ ነው አነስተኛ ግን እጅግ ትርጉም ያለው የPulse of Africa ጅማሮ በመጪዎቹ ጊዜያት ከፍ ወዳለ መሪ አኅጉራዊ ሚዲያ የማደግ መንገድ እጅግ ጠቃሚ የሚሆነው ሲሉም ገልጸዋል።
አፍሪካ ዐቢይ የኢንዱስትሪ ማዕከል እና የዓለም ቁልፍ ሚና ተጫዋች የመሆን መንገድ ላይ በማያጠራጥር መንገድ እየተጓዘች ትገኛለች ሲሉም አረጋግጠዋል።
የPulse of Africa ሚዲያ መቋቋም ወደፊት የመመልከት ርምጃ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዓለም መድረክ ጠንካራ እና ቱባ የአፍሪካ ድምፅ የማሰማት መሠረትም ነው በማለት ገልጸዋል።