የድሬዳዋ ጤና ቢሮ የደም እና ህብረ-ህዋስ ባንክ ዘመናዊ የደም ተላላፊ በሽታዎች መመርመሪያ ማሽኖችን ስራ አስጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የድሬዳዋ ጤና ቢሮ የደም እና ህብረ-ህዋስ ባንክ ዘመናዊ የደም ተላላፊ በሽታዎች መመርመሪያ ማሽኖችን ስራ አስጀመረ
ድሬዳዋ፤ መስከረም 27/2018(ኢዜአ)፡- የድሬዳዋ ጤና ቢሮ የደም እና ህብረ-ህዋስ ባንክ ዘመናዊ የደም ተላላፊ በሽታዎች መመርመሪያ ማሽኖችን አስመርቆ ስራ አስጀመረ።
አስተዳደሩ በዛሬው እለት ዘመናዊ የደምና የህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት የተቀናጀ ህንፃ ግንባታንም አስጀምሯል።
ከመቶ ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ለሚገነባው የደም እና ህብረ-ህዋስ ባንክ የመሠረት ድንጋይ ያስቀመጡት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሳህረላ አብዱላሂ እና የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ናቸው።
አገልግሎት እየሰጠ ለሚገኘው የድሬዳዋ ጤና ቢሮ የደም እና ህብረ-ህዋስ ባንክ በ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር የተገዙ ዘመናዊ የደም ተላላፊ በሽታዎች መመርመሪያ ማሽኖች ናቸው ተመርቀው ስራ የጀመሩት።
ሚኒስትር ዴኤታዋ በወቅቱ እንዳሉት፤ ዘመናዊ ማሽኖቹ የደምና ህብረ ህዋስ አገልግሎቶችን ቀልጣፋና ውጤታማ ለማድረግ ያስችላሉ።
ከንቲባ ከድር ጁሃር በበኩላቸው ዛሬ ግንባታው የተጀመረው የደምና ህብረ ህዋስ ህንፃ በፍጥነትና በጥራት እንዲጠናቀቅ በማድረግ የተሻለ የጤና አገልግሎት የመስጠቱ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በሚኒስትር ዴኤታዋ የተመራው የዘርፉ አመራር ቡድን የተሳተፈበት 13ኛው የደምና ህብረ ህዋስ ባንኮች ዓመታዊ ጉባኤ "ዲጂታላይዜሽንና ፈጠራ ለጠንካራ የደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት" በሚል መሪ ሃሳብ በዛሬው ዕለት መካሄድ ጀምሯል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ፅጌረዳ ክፍሌና የኢትዮጵያ ደምና ህብረ ህዋስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አሸናፊ ታዘበውን ጨምሮ የፌዴራልና የአስተዳደሩ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።