በዞኑ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የትምህርት ቤቶች እና ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች ግንባታ ተከናውኗል - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የትምህርት ቤቶች እና ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች ግንባታ ተከናውኗል
ነገሌ ቦረና ፤ መስከረም 27/2018(ኢዜአ)፡- በምስራቅ ቦረና ዞን በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች እና ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች ግንባታ በትኩረት መከናወኑ ተገለጸ።
በዞኑ ባለፈው ሀምሌ ወር የተጀመረው ሁለንተናዊ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉ ተመልክቷል፡፡
የምስራቅ ቦረና ዞን ገንዘብ እና ኢኮኖሚ ጽህፈት ቤት የህዝብ ተሳትፎ ቡድን መሪ አቶ አንድነት አበበ እንደገለጹት የዞኑ በጎ ፈቃደኞች በ7 ዋና ዋና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዘርፎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እያከናወኑ ነው፡፡
በዞኑ ነገሌ ቦረና ከተማን ጨምሮ በ9 ወረዳዎች ከ40 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኞች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ገልጸው ዘርፎቹም ግብርና፣ ትምህርት፣ ጤና፣ የከተሞች ጽዳትና ውበት፣ ደም ልገሳ እና አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከባለፈው ሀምሌ ወር ጀምሮ እስካሁንም የ27 ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችና 129 የመማሪያ ክፍሎች መገንባታቸውን ገልጸው የከተሞች ጽዳትና ውበት በበጎ ፈቃደኞች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ለዞኑ አረጋዊያንና አቅመ ደካሞች 736 አዲስ የመኖሪያ ቤቶች እየተገነቡ ሲሆን 440 ቤቶች በእድሳት ላይ እንዳሉ አስታውቀዋል፡፡
የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ ድጋፍ እንዲሁም ለአቅመ ደካሞች የወተት ላም፤ በግና ፍየል፤ የምግብ እህልና ዘይት ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም እንዲሁ።
በከተማው የሀሎ ጋፍትሮ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ሰለሞን ሀይሌ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመሳተፍ ላይ ካሉ ነዋሪዎች መካከል አንዱ ናቸው፡፡
ከሌሎች በጎ ፈቃደኞች ጋር በመሆን ለ3 አረጋዊያን አዲስ ቤት መስራታቸውንና ለ96 ህጻናት የተለያዩ የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል፡፡
የዚሁ ከተማ ነዋሪ አቶ ዳዊት ሀብተሚካኤል ከበጎ ፈቃደኞች ባሰባሰቡት 91 ሺህ ብር ለአረጋዊያን ቤት ከመስራት ባለፈ አልባሳት፤ የምግብ እህልና ዘይት ድጋፍ አድርገዋል፡፡
በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል የነርቭ ህመም ታማሚ ህጻን አሳዳጊ የሆኑት ወይዘሮ ወይንሸት ኩማ፣ ''በበጎ ፈቃደኞቹ አዲስ ቤት ተሰርቶልኛል፣ የምግብ እህልና ዘይት ድጋፍም አግኝቻለሁ'' ብለዋል።
ለተደረገላቸው ድጋፍ በጎ ፈቃደኞችን አመስግነው፤ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚደረግ ሰብዓዊ ድጋፍ ባህል ሆኖ ሊቀጥል ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።