የአፍሪካ ህብረት የወጣቶችን ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ስራውን አጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ህብረት የወጣቶችን ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ስራውን አጠናክሮ ይቀጥላል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 27/2018 (ኢዜአ)፦ የአፍሪካ ህብረት የአህጉሪቷ ወጣቶችን ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ስራውን ይበልጥ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኑን አስታወቀ።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሐመድ አሊ ዩሱፍ ከፓን አፍሪካ የወጣቶች ህብረት ከፍተኛ አመራሮች ከሆኑት ዲያላ ሞሙኒ እና አህመድ ቤኒንግ ጋር በአዲስ አበባ ውይይት አድርገዋል።
ውይይቱ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን እና የፓን አፍሪካ ወጣቶች ህብረት በትብብር መስራት የሚያስችላቸውን የጋራ መግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።
የአፍሪካ ህብረት የወጣቶች ልዩ የቴክኒክ ኮሚቴ ሊቀ መንበር ኡቺዚ ምካንዳዋየር በስምምነት ስነ ስርዓቱ ላይ ተገኝተዋል።
የአፍሪካ ህብረት ስምምነቱ የአህጉሪቷ ወጣቶች ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እና ወጣቶችን ለማብቃት ያለውን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ ገልጿል።
በስምምነቱ አማካኝነት የፓን አፍሪካ የወጣቶች ህብረት በሀገራት ደረጃ ያሉ የወጣት ምክር ቤቶች የሚያቀናጅ አህጉራዊ ማዕቀፍ እና ለአፍሪካ ወጣቶች እንደ ጋራ ድምጽ ሆኖ የሚያገለግል መሆኑን ኢዜአ ከህብረቱ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
የፓን አፍሪካ የወጣቶች ህብረት የፓን አፍሪካ ወጣቶች ህብረት ንቅናቄ የወለደው አህጉራዊ አደረጃጀት ሲሆን እ.አ.አ በ1962 የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች በጊኒ ኮናክሪ ባደረጉት ስብስባ ህብረቱን አቋቁመዋል።
ህብረቱ የተመሰረተው በወቅቱ ወጣቶች አፍሪካ ከቅኝ ግዛት እንድትላቀቅ ለነበረው ትግል አቅም እንዲሆኑ ከማሰብ የመነጨ ነው።
የወጣቶች ህብረቱ እንቅስቃሴ የፖለቲካ ድጋፍን በማሰባሰብ እና የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ ግዛት ነጻ እንዲወጡ በማድረግ ረገድ ስትራጂካዊ ሚናውን ተጫውቷል።
የአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት እ.አ.አ በ2006 ባደረገው ስብስባ የፓን አፍሪካ ወጣቶች ህብረት በድጋሚ የማደራጀት የውሳኔ ሀሳብ በማፅደቅ ህብረቱ የአህጉሪቷ የወጣት መዋቅር እንዲሆን በይኗል።