በክልሉ የሚያጋጥምን የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል አቅም እየተፈጠረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የሚያጋጥምን የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል አቅም እየተፈጠረ ነው
ወላይታ ሶዶ፤መስከረም 26/2018(ኢዜአ):- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚያጋጥምን የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል አቅም እየተፈጠረ መሆኑን የክልሉ መንግስት ዋና ተጠሪ ገብረመስቀል ጫላ ገለጹ።
በወላይታ ዞን ካዎ ኮይሻ ወረዳ ከዚህ ቀደም በመሬት መንሸራተት ምክንያት ከቀያቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን በአበላ አባያ ወረዳ የማስፈር መርሃ ግብር ተካሂዷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የክልሉ መንግስት ዋና ተጠሪ ገብረመስቀል ጫላ፤ በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች የተፈናቀሉ ወገኖችን ከስጋት ነፃ በሆኑ አካባቢዎች የማስፈርና በዘላቂነት የማቋቋም ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም በክልሉ የሚያጋጥምን የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል አቅም እየተፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ መሪሁን ፍቅሩ (ዶ/ር)፤ የክልሉ መንግስት በጎፋ ዞን በደረሰ የመሬት መንሸራተት አደጋ የተፈናቀሉ ወገኖችን ለማቋቋም በሰራቸው ስራዎች የተረጋጋ ኑሮ መምራት መጀመራቸውን ገልጸዋል።
በዛሬው ዕለትም በወላይታ ዞን በካዎ ኮይሻ ወረዳ በተመሳሳይ ችግር ከቀያቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን በምቹ አካባቢዎች የማስፈርና በዘላቂነት የማቋቋም ስራ መከናወኑን ጠቅሰዋል።
የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ሳሙኤል ተሰማ (ረዳት ፕሮፌሰር)፤ በዛሬው ዕለት እነዚህን ወገኖች ለማቋቋም የሚያስችል ስራ ተጠናቅቆ ወደ ማስፈር መገባቱን ጠቅሰው የተለያዩ ባለድርሻዎች በማሳተፍ የመኖሪያ ቤትና ሌሎች ቁሶች መሟላታቸውን ተናግረዋል።
በነበረው የተፈጥሮ ችግር የተፈናቀሉና አሁን ላይ በምቹ አካባቢዎች የሰፈሩ ወገኖችም የክልሉ መንግስት ላደረገላቸው አስተዋጽኦ አመስግነው ለነገ የተሻለ ህይወት ሰርተው ለመቀየር መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።