የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎችን የመከላከልና ፈጣን ምላሽ የመስጠት አቅም እየተጠናከረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎችን የመከላከልና ፈጣን ምላሽ የመስጠት አቅም እየተጠናከረ ነው
ሀዋሳ፤ መስከረም 26/2018(ኢዜአ)፡- በሲዳማ ክልል የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎችን የመከላከልና ፈጣን ምላሽ የመስጠት አቅም እየተጠናከረ መሆኑን የክልሉ ምክትል ርእሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ በየነ በራሳ ገለጹ።
በክልሉ የእሳት አደጋ ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ የፖላንድ መንግስት የ5 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸውን የተለያዩ ቁሳቁሶች ድጋፍ አድርጓል።
የተደረገውን ድጋፍም የክልሉ ምክትል ርእሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ በየነ በራሳ ተረክበዋል።
ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ በክልሉ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎችን የመከላከልና ፈጣን ምላሽ የመስጠት አቅም እየተጠናከረ መምጣቱን ገልጸዋል።
በዘርፉ ጥረት የአጋር አካላት ትብብርና ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን አንስተው በፖላንድ መንግስት የተደረገው ድጋፍ ተጨማሪ አቅም ይሆናል ብለዋል።
የክልሉ ከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ምክትል ሃላፊ መድሃኒት ከበደ፤ በክልሉ አደጋን ለመከላከል የሚያስችል የዳበረ አቅም ለመፍጠር የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የተጀመረውን ቅንጅታዊ ስራ በማጠናከር በክልሉ እያደገ የመጣውን የኢንቨስትመንት ፍሰት ታሳቢ ያደረገ የአደጋ መከላከልና መቆጣጠር ጥረት ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አረጋግጠዋል።
በኢትዮጵያ የፖላንድ ኤምባሲ ጊዜያዊ የሚሲዮን መሪ ኢሎና ኮርቹት፤ በኢትዮጵያ በፍጥነት እያደገ ያለውን የምጣኔ ሃብት እድገት የሚመጥን የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም የተደረገው ድጋፍ ለድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ የሚሰጥና ለመከላከል ስራዎች የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።