ኢትዮጵያ በጠንካራ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ያላትን ተደማጭነት እና ሚና ማሳደግ ችላለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በጠንካራ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ያላትን ተደማጭነት እና ሚና ማሳደግ ችላለች
አዲስ አበባ፤ መስከረም 26/2018(ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያ በጠንካራ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ያላትን ተደማጭነት ማሳደግ እና የባህር በር የማግኘት ተፈጥሯዊ መብቷን ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እንዲኖረው ማድረግ መቻሏን የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ገለጹ፡፡
6ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል፡፡
የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በሁለቱ ምክር ቤቶች የመክፈቻ ሥነ-ስርዓት ባደረጉት ንግግር፤ የኢትዮጵያ ውጭ ግንኙነት ማዕከልና መሠረታዊ ማጠንጠኛው ብሔራዊ ጥቅምና የዜጎች ክብር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የሀይል አሰላለፎች ሚዛን በመጠበቅ በትብብርና የጋራ ተጠቃሚነት መርህ እንደምትሰራ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያን ውጭ ግንኙነት ስትራቴጂያዊ ምርጫም ከታዛቢነት ወደ አጀንዳ ተላሚነትና ተፅዕኖ ፈጣሪነት ማሸጋገር ተችሏል ብለዋል፡፡
በዓለም መድረኮች ዘንድ ያላትን ተሳትፎና ተደማጭነት በማስፋት የጋራ ተጠቃሚነትን ለማሳደግና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ለይ ወሳኝ ሚና ለመጫወት በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ሰላምና ደህንነትን ለማስጠበቅ፤ እድገትና ብልጽግናን የምታረጋግጠው በዓለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ተፅዕኖ ማሳረፍ ስትችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ለዚህ ደግሞ የሀገርን ዳር ድንበር ከማስጠበቅ ባሻገር የዜጎችን መብትና ክብር በማስጠበቅ ሰውን ማዕከል ያደረገ ብሔራዊ ደህንነትን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል፡፡
በዚህም የዜጎችን ክብርና ደህንነት የብሔራዊ ደህንነት አጀንዳ በማድረግ በውጭ ሀገራት ለእንግልትና ለችግር የተጋለጡ ዜጎች በክብር ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ መደረጉን አንስተው፤ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ከኩስመና ወደ ተለወጠ ቁመና መለወጡን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ ከማህጸኗ በፈለቁ ወንዞች ፍትሐዊ ተጠቃሚ የመሆኗን ያህል አስተማማኝ የባህር በር ትፈልጋለች ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በዓባይና ቀይ ባህር መካከል የምትገኝ ሀገር መሆኗን በማንሳት፤ ከሁሉቱም ውሃዎች በኢ-ፍትሐዊነት ተገልላ የቅርብ ሩቅ ሆና መቆየቷን ገልጸዋል፡፡
በዓባይ ወንዝ እና በቀይ ባህር ዙሪያ በተደረገው ያልተቋረጠ ጥረት ህዳሴ ግድብን ከቀውስ በመታደግ ማጠናቀቅ፣ የባህር በር የማግኘት ተፈጥሯዊ መብት በጎረቤትና በዓለም ሀገራት ዘንድ ቅቡልነት እንዲያገኝ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም በሁለቱ ውኃዎች ላይ የኢትዮጵያን የመልማት ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ ትስስርና ትብብር ለመፍጠር ሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ቅድሚያ ለጎረቤት የሚሰጥ መሆኑን ያነሱት ፕሬዝዳንቱ፤ ይሄውም ባለፉት ዓመታት በተግባር የተገለጠ መርህ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ከጎረቤት ሀገራት ጋር ትብብርና ትስስር በመፍጠር ችግሮች ግጭት ሳይፈጠር በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ስታደርግ ቆይታለች ብለዋል፡፡
ቀጣናውን የሚያስተሳስሩ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች ሲከናወኑ እንደነበር አስታውሰው፤ ኢትዮጵያ መልካም ጉርብትና በመፍጠር ለቀጣናው ሰላም ኢኮኖሚያዊ ትስስር አበክራ እንደምትሰራ ገልጸዋል፡፡