ቀጥታ፡

የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የሚከናወኑ ተግባራት ስኬታማ እንዲሆኑ የበኩላችንን እንወጣለን 

ገንዳ ውሃ ፤ መስከረም 26/2018(ኢዜአ)፡-ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠርና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የሚከናወኑ ተግባራት ስኬታማ እንዲሆኑ የበኩላቸውን  እንደሚወጡ የምዕራብ ጎንደር ዞን የመንግስት ሠራተኞች ገለጹ። 

ለልማት ሥራዎች በገንዘብ፣ በእውቀትና በጉልበት የሚያደርጉትን ድጋፍ እንደሚያጠናክሩም ሠራተኞቹ ተናግረዋል።

በምዕራብ ጎንደር ዞን አስተዳደር የመንግስት ሠራተኞች "የታደሰ ጂኦስትራቴጂያዊ ቁመና፣ በሁሉም ኢትዮጵያዊያን የጋራ ትጋት" በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ በየክላስተሩ ውይይት አካሂደዋል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ጌጡ አስማማው እንደገለጹት፣ ውስጣዊ አንድነትን በማጎልበት ልማትን ለማፋጠን የሚከናወኑ ተግባራትን አጠናክሮ ለማስቀጠል እንደሚሰሩ ገልጸዋል። 

በተለይ ገዥ ትርክትን በዜጎች ላይ በማስርጽ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠርና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የሚከናወኑ ተግባራት ስኬታማ እንዲሆኑ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል። 

ለዜጎች ቀልጣፋና ፍትሃዊ አገልግሎት በመስጠት ህዝባዊ እርካታን ለመፍጠር በቁርጠኝነት እንደሚሰሩም ነው አቶ ጌጡ የገለጹት።

ሌላኛው የመድረኩ ተሳታፊ አቶ ግርማ ሲሳይ በበኩላቸው የዞኑን ህዝብ የልማት ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ዘላቂ ሰላም ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፣ የአካባቢውን ሰላምና የህዝቦችን አንድነት የማጠናከር ሃላፊነታቸውን ለመወጣት ተግተው እንደሚሰሩም ተናግረዋል።


 

ሀገራዊ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችና በዞኑ የሚካሄዱ የልማት ሥራዎች ከዳር እንዲደርሱ በገንዘብ፣ በእውቀትና በጉልበት የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ እንደሚያጠናክሩም አረጋግጠዋል። 

ከዚህ በተጨማሪ የዜጎችን አብሮነት የሚያሰርጹ ገዥ ትርክቶች እንዲጎለብቱ የድርሻቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል። 

የምዕራብ ጎንደር ዞን ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ አቶ መሰንበት መልካሙ እንዳሉት ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ  ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም የመፈፀም ብቃት አድጓል። 


 

ይህን አጠናክሮ ለማስቀጠል በአብሮነት ግንባታቸው የተጀመሩና የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠላቸው የልማት ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ማጠናቀቅ ይገባል ብለዋል።

በተለይ የመንግስት ሠራተኛው ለዜጎች ፈጣን፣ ውጤታማና ፍትሃዊ አገልግሎት በመስጠት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከመፍታት ባለፈ የልማት ሥራዎች ከዳር እንዲደርሱ ሃላፊነቱን በብቃት እንዲወጣም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም