ቀጥታ፡

በእውቀትና ክህሎት የዳበረ ትውልድ በመፍጠር ሂደት የመምህራን የላቀ ሚና ተጠናክሮ ይቀጥላል

አዳማ ፤ መስከረም 26/2018(ኢዜአ)፡- በእውቀትና ክህሎት የዳበረ ትውልድ በመፍጠር ሂደት የመምህራን የላቀ ሚና ተጠናክሮ እንደሚቀጥል  የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ገለጸ።

ዓለም አቀፉ የመምህራን ቀን “በአንድነት ለመምህራን፣ በአንድነት ለመጪው ጊዜ” በሚል መሪ ሃሳብ በአዳማ ሣይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የምርምር መድረክ ተካሂዷል።


 

በዚሁ መድረክ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ፕሬዝዳንት ዮሐንስ በንቲ (ዶ/ር)፤ በትውልድ ግንባታ ለሀገር ፅኑ መሰረት በማኖር ሂደት መምህራን የማይተካ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል።

የመምህራንን አቅም በማጎልበት ጭምር የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ መንግስት እያደረገ ያለውን ጥረት አንስተው በሁሉም ረገድ የትምህርት ዘርፉን ማጠናከር ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል።

በእውቀትና ክህሎት የዳበረ ትውልድ በመፍጠር ሂደት የመምህራን የላቀ ሚና ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል። 

በትምህርት ሚኒስቴር የመምህራንና የትምህርት አመራሮች ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ሙሉቀን ንጋቱ (ዶ/ር) ለትምህርት ጥራትና ተደራሽነት መንግስት በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በዚህ ረገድ የመምህራንን አቅም በማጠናከርና በሰው ሃብት ልማትና የተሟላ የሰው ሃይል እንዲኖር ከማድረግ አንፃር በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተዋል።

የአዳማ ሣይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ለሚ ጉታ (ዶ/ር)፤ የትምህርት ዘርፍ መጠናከር ለአንድ ሀገር እድገትና ማንሰራራት ወሳኝ መሆኑን አንስተው በዚህ ረገድ የመንግስት ጥረት የሚደነቅ ነው ብለዋል።


 

ለትምህርት ዘርፉ እድገት የመንግስት ጥረት ብቻውን በቂ ባለመሆኑ በተለይም መምህራን፣ ወላጆችና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጥረት ሊጠናከር እንደሚገባም አንስተዋል።

በዓለም የመምህራን ቀን ተሰይሞ ምስጋና እና እውቅና መቸሩ ተገቢ መሆኑን ገልጸው፤ ለመምህራን ሁሉም ክብርና አድናቆት  መስጠት እንዳለበት ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም