የአንጎል ዕጢ ያለበት ሰው ማድረግ ያለበት ጥንቃቄ … - ኢዜአ አማርኛ
የአንጎል ዕጢ ያለበት ሰው ማድረግ ያለበት ጥንቃቄ …
አንጎላችን የሰውነታችን መሪ ወይም መተግበሪያ ኮምፒውተር ነው ይላሉ የሕክምና ባለሙያዎች።
በቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ኒዩሮ ሰርጂን እና የሕጻናት የነርቭ ቀዶ ሕክምና ሰብ ስፔሻሊስት ዶክተር ያሬድ ንጉሴ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ከአንጎል ዕጢ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ሙያዊ ገለጻ አድርገዋል።
👉 የአንጎል ዕጢ ምንድን ነው?
ዶክተር ያሬድ እንዳሉት፤ ከመደበኛ መንገድ ውጭ የሚበዙ እና የራሳቸውን የመባዣ መንገድ የሚከተሉ ኅዋሳት በአንጎል ውስጥ የሚፈጥሩት እብጠት የአንጎል ዕጢ ይባላል።
እነዚህ ኅዋሳት ጤናማ እንዳልሆኑ ገልጸው፤ ለአብነትም አንጎላችንን በመጫን ወይም የአንጎል ግንኙነት ሥርዓት በመቀነስ የተለመዱ ሥራዎችን እንዳይፈጽም ያደርጋሉ ብለዋል። ይህ ሂደትም አንጎላችን በብዙ መልኩ እንዲጎዳ ያደርጋል ነው ያሉት።
👉 የአንጎል ዕጢዎች ዓይነት
በዋናነት የአንጎል ዕጢዎች ገር (Benign Tumor) እና አደገኛ (Malignant Tumor) ተብለው እንደሚከፈሉም ዶክተር ያሬድ አስረድተዋል።
1ኛ. ገር ዕጢ (Benign Tumor)፡- እንደ ባለሙያው ገለጻ ይህ የዕጢ ዓይነት በፍጥነት አይራባም (አያድግም)፤ በሰውነት ሌሎች ክፍሎች ላይም አይስፋፋም።
ነገር ግን በአንጎል ውስጥ ቦታ ስለሚይዝ ከተወሰነ ደረጃ በላይ ቢያድግ ችግር ሊፈጥር ይችላል ያሉት ዶክተር ያሬድ፤ አብዛኛውን ጊዜ በቀዶ ጥገና ሕክምና ሙሉ በሙሉ ይወገዳል ብለዋል።
2ኛ. አደገኛ ዕጢ (Malignant Tumor)፡- ይህኛው የዕጢ ዓይነት በፍጥነት ያድጋል፤ በአንጎል አቅራቢያ ወዳሉ ቦታዎችም ይስፋፋል ይላሉ።
እጅግ አደገኛ ዕጢ መሆኑን ጠቅሰው፤ አንዳንድ ጊዜ “የአንጎል ካንሰር” ተብሎ እንደሚጠራም አስረድተዋል። ይህን ዕጢ ለማከምም የበለጠ ውስብስብ ሕክምና ያስፈልገዋል ነው ያሉት።
👉 የአንጎል ዕጢ መንስዔ እና ተጋላጮች
የአንጎል ዕጢ የሚፈጠርበት ምክንያት በውል (ሙሉ በሙሉ) እንደማይታወቅ የጠቀሱት ዶክተር ያሬድ፤ ነገር ግን አንዳንድ አጋላጭ ምክንያቶች ያሉበት ሰው የአንጎል ዕጢ የማጋጠም ዕድሉ ከሌሎች አንጻር ከፍ ያለ መሆኑን አስገንዝበዋል። እነዚህ አጋላጭ ምክንያቶችም፡-
• በቤተሰብ ውስጥ የአንጎል ዕጢ ያጋጠማቸው ሰዎች መኖር፤
• ለከፍተኛ ጨረር (Radiation) በተደጋጋሚ መጋለጥ፤ (ለሕክምና የሚወሰደው ጨረር በጣም ዝቅተኛ እና አደጋ አልባ መሆኑን አስገንዝበዋል)።
• የዕድሜ ሁኔታ (የአንጎል ዕጢ በየትኛውም ዕድሜ እንደከሚከሰት ጠቅሰው፤ በተለይም በልጅነት እና በሽምግልና የዕድሜ ክልል ላይ ያሉ ሰዎች ተጋላጭ መሆናቸውን ገልጸዋል።)
👉 የአንጎል ዕጢ ምልክቶች
ዕጢው እንደተከሰተበት የአንጎል ክፍልና ያለበት የህመም ደረጃ ምልክቶቹ እንደሚለያዩ ዶክተር ያሬድ ያስገነዝባሉ። በዚህም መሠረት፡-
• የራስ ህመም (Headache) (በጣም ጠንካራ እና በተደጋጋሚ የሚስተዋል)፤
• የሚጥል በሽታ (Seizures)፤
• የዐይን የማየት ዐቅም መቀነስ፤
• የማሰብ እና የማስታወስ ችግሮች (ቀላል ነገሮችን መርሳት፣ ትኩረት ማድረግ አለመቻል)፤
• የሰውነት ክፍል አለመታዘዝ (ለምሳሌ አንድ እጅ ወይም እግር አለመንቀሳቀስ)፤
• ለመናገር መቸገር (ቃላትን በአግባቡ አሰናስሎ በትክክል መናገር አለመቻል) እንዲሁም
• የፀባይ ለውጥ መኖር (ያልተለመደ ስሜታዊነት፣ ብስጭት) የሚሉት ምልክቶች ሲስተዋሉ ወደ ሕክምና ተቋም በመሄድ ተገቢውን ምርመራ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
👉 የአንጎል ዕጢን ለመከላከል
ዶክተር ያሬድ እንዳሉት፤ የአንጎል ዕጢ እንዳይከሰት ሙሉ በሙሉ ለመከላከል የተወሰነ መንገድ ባይኖርም ጤናማ የኑሮ ዘይቤን መከተል ተጋላጭነትን ይቀንሳል። በዚህም መሠረት፡-
• ጤናማ አመጋገብን ማዘውተር፤
• ስፖርታዊ እንቅስቃሴን ባህል ማድረግ፤
• አልኮል አለመጠጣት፤
• ሲጋራ አለማጨስ፤
• ከጨረር (Radiation) እና አደገኛ ኬሚካሎች (pesticides) መራቅ እንደሚገባ መክረዋል።
👉 የአንጎል ዕጢ ታማሚ ማድረግ ያለበት ጥንቃቄ እና ሕክምናው
የሕክምና ባለሙያው እንዳሉት፤ አንድ ሰው በሕክምና ምርመራ የአንጎል ዕጢ እንዳለበት ሲረጋገጥ መደናገጥ የለበትም። የሕክምና ሂደቱን ግን በጥብቅ መከታተል ይጠበቅበታል። በዚህምመሠረት፡-
• የሕክምና ባለሙያን ምክር በንቃት እና በትጋት መተግበር፤
• ሕክምናው እንደ ዕጢው ዓይነት እና የህመም ደረጃ እንደሚወሰን አስገንዝበዋል። በመሆኑም የመድኃኒት (Chemotherapy)፣ የጨረር እና የቀዶ ጥገና ሕክምናዎች እንደ ሁኔታው እንደሚሰጡ አብራርተዋል።
• ጤናማ አመጋገብ እና የኑሮ ዘይቤን መከተል፤ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ማዘውተር፤ አልኮልና ሲጋራ አለመውሰድ (እየወሰዱ ከሆነ ማቆም)፤
• ለብቻ በውጥረት መብሰልሰልን ማቆም፤ (ሐሳብን ወይም ስሜትን ለሌሎች ማጋራት እጅግ አስፈላጊ ነው።)
• ሁሌም አዎንታዊ አስተሳሰብን ማስቀደም፤ በዚህ ህመም ተጠቅተው በሕክምና ከተረዱ በኋላ ጤናማ ሆኖ መኖር እንደሚቻል መገንዘብ ይገባል ይላሉ ባለሙያው።
👉 የአንጎል ዕጢ ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ
የአንጎል ዕጢ በጣም አልፎ አልፎ የሚከሰት በሽታ ነው ማለት አይቻልም ያሉት ዶክተር ያሬድ፤ በዓመት ከ100 ሺህ ሰዎች መካከል ከ10 እስከ 15 ያህሉ በአንጎል ዕጢ ይጠቃሉ። በሁሉም የዕድሜ ክልል እና ጾታ ሊከሰት ይችላል ብለዋል።